አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከ 2ሺህ 50 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ነው

397

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከ 2ሺህ 50 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ገለጸ።

በአገራዊ ምክክሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ባለሥልጣኑ ገልጿል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ ባለፉት ሦስት ዓመታት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከለውጡ በፊት በነበረው አዋጅ የመደራጀት መብት፣ የልማት አጋርን ማፈላለግና ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያጎሉ ተግባራት ላይ መሳተፍ አዳጋች እንደነበር አስታውሰዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻልና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ድርጅቶቹ የተቋቋሙበትን ሕግን ማሻሻል አስፈላጊ እንደነበር ጠቁመዋል።

በዚህም ድርጅቶቹ በነጻነት እንዲሳተፉ የሚያደርጉ 17 መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ነው ያነሱት።

ከዚህም ውስጥ አራቱ መመሪያዎች ጸድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውንና አምስት መመሪያዎች ደግሞ በቅርቡ እንደሚጸድቁ ይጠበቃል ብለዋል።

ሰባት መመሪያዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን አንድ መመሪያ  የመጨረሻ ማስተካከያ እየተደረገበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህንን ተከትሎ በአገሪቱ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ሶስት ዓመታትም ከ2 ሺህ 50 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከዚህ ውስጥ 524ቱ በ2014 ዓ.ም ብቻ የተመዘገቡ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

እነዚህም ድርጅቶች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ኃብት በማሰባሰብ በችግር ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲያጎለብቱ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

በዋናነትም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ስለ አገራዊ ምክክሩ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል  ሥልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሚያወጣቸው እቅዶች ላይ በመመሥረትም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶች መካሄዳቸውንም አንስተዋል።

ድርጅቶችም አገራዊ ምክክሩን ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጁ መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም