መንግሥት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት የሚያረጋግጡ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተሰራ ነው

29

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) መንግሥት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት የሚያረጋግጡ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እንዳለው መኮንን ይህን ያሉት “አክሪዲቴሽን ለአካባቢ እና ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ” በሚል መሪ  ሀሳብ 12ኛውን  የአክሪዲቴሽን ቀን በማስመልከት በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ ነው።

በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶች የጥራት ደረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ በኢኮኖሚው እድገት ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

መንግሥት የምርት ጥራትን ለማሻሻል በሰጠው ልዩ ትኩረት የጥራት ማረጋገጫ ተቋማትን ለማዘመን ከ3  ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ዘመናዊ ላቦራቶሪ የማሟላትና ሌሎች የግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪ ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለጥራትና ደረጃዎች ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የአገልግሎት መስጫ ግንባታዎች እንዲሁም ለሰራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ገበያና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ተወዳዳሪ ሆነው ገዥ የሚያገኙት ጥራትና ደረጃቸውን ሲጠብቁ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በመሆኑም የግልና የመንግሥት ተቋማት ለሚያመርቷቸው ምርቶች የጥራት ማረጋገጫ የሚያስገኝ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ምክትል  ዋና ዳይሬክተር ጌትነት ጽጌመላክ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከ2003  ዓ.ም ጀምሮ ለ96 ተቋማት የጥራት ሰርተፊኬት አገልግሎት መስጠቱን ነው የተናገሩት።

የአክሪዲቴሽን ዕውቅና በየዓመቱ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለህክምና ላቦራቶሪዎች፣ ለተለያዩ የውሃ፣ የአፈር፣  የድምፅ ብክለት ፍተሻ  የሚያደርጉ ላቦራቶሪዎችና  መሰል ተቋማት የጥራት ሰርተፊኬት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚሁ ዝግጅት  ላይ  “አክሪዲቴሽን አካባቢና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት”  እንዲሁም “የአካባቢ ብክለት በኢትዮጵያ” በሚሉ ርዕሰ ጉዳች ላይ  ጥናታዊ ጽሑፎች  ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡