ባለሥልጣኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን ሥምምነት ተፈራረመ

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጋር አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ።

ሥምምነቱን የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወልደአብ ደምሴና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ፈርመውታል።

ሥምምነቱን ባለሥልጣኑ የሚያከናውነው የመንግሥት የግዢ ሥርዓት በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት የታገዘና ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተገልጿል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወልደአብ ደምሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሥምምነቱ የመንግሥት የግዢ ሥርዓት በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት የታገዘ ለማድረግ ያስችላል።

ያም ብቻ ሳይሆን በግዢ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለልና ለመከላከል እንደሚረዳም ጠቁመዋል።  

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ያቀላጥፋል ብለዋል።

ተቋማቸውም የሳይበር ደኅንነት አደረጃጀት እንዲዋቀርና አስፈላጊው መመሪያ እንዲያዘጋጅ የሚያስችል የማማከር ሥራ እንደሚያቀርብም ነው የተናገሩት።    

ይህም የመንግሥት በጀት አጠቃቀም ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አገልግሎት ላይ እንዲውል በማድረግ የአገሪቷን ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም