ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አገራዊ አቅምን ሊያጠናክሩ ይገባል

99

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አገራዊ አቅምን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

"የኢንተርፕራይዝ ሽግግር፣ ለኢንዱስትሪ መሠረት" በሚል መሪ ኃሳብ የ11ኛ ዙር ኢንተርፕራይዞች የምርቃ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በ11ኛው ዙር 169 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል ተብሏል።

ኢንተርፕራይዞቹ ባስመዘገቡት ካፒታል፣ በፈጠሩት የሥራ ዕድል፣ በተጠቀሙት ቴክኖሎጂና ባሳዩት የፈጠራ በቃትን ወደ መካከለኛ ደረጃ መሸጋገራቸው ተጠቅሷል።

ከእነዚህም 84ቱ በማኑፋክቸሪንግ፣ 77 በኮንስትራክሽን፣ 4ቱ በንግድ፣ 3ቱ በአገልግሎትና ሁለት ደግሞ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ናቸው ተብሏል።

ባለፉት 10 ዙሮች 1 ሺህ 456 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ መሸጋገራቸውም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩት መንግሥት ድጋፍና በኢንተርፕራይዞቹ ጥረት ነው።

በቀጣይም ኢንተርፕራይዞቹ የሚያጋጥማችውን የተለያዩ ተግዳሮት በመቋቋምና ጥረታችውን አጠናክረው በመቀጠል በዘርፋቸው ምርትና ምርታማነታቸው ማሳደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።  

በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገውን አገራዊ ጥረት በመደገፍ አገራዊ የማምረት አቅምን ለማሳደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ አገራዊ አቅም እንዲሆኑ የተቀመጠውን ግብ እንዲያሳኩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከንቲባ አዳነች ጠይቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም