ሕዝቡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግና የመብት ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል

4

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) ሕዝቡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግና የመብት ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ካደረጉት መካከል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አሥራት አጸደወይን እንደገለጹት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

እንደ እሳቸው ገለጻ በዚህ ወቅት በአገሪቷ ከፍትህ ጋር የተያያዙ፣ ጽንፈኝነትና አክራሪነት የመሳሰሉ ‘ከኔነት ስሜት’ የሚመነጩ ችግሮች ይስተዋላሉ።

እነዚህ ጉዳዮች መጨረሻቸው ወደ ግጭት ካመራ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈጸሙ ዕድል ይፈጥራል ባይ ናቸው።

በመሆኑም ሰብዓዊ መብት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃውም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

ሌላው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ሕብረት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስዑድ ገበየሁ እንደሚሉት ለሰብዓዊ መብት መከበር በአንድነት በመቆም ያስፈልጋል።

የሰብዓዊ መብቶች ከመጣሳቸው በፊት ጥብቅ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የመብት ጥሰት የፈጸሙ አካለት ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት መከበር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው በሰብዓዊ መብት ዙሪያ አስፈላጊውን ትምህርት በማስተማር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ትምህርት ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

”ኮሚሽኑ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ዋነኛውና ትልቁ የሰብዓዊ መብቶች ግንዛቤን በህብረተሰቡ ውስጥ ማስፋፋት ነው” ብለዋል፡፡

በተለይም ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ትምህርቶች በስፋት በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ የሚደረግ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ደግፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ መብራቱ አክለውም ወጣቶችን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በየጊዜው የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለይቶ ለህዝብ ከመግለጽ ባለፈ የሚመለከታቸው አካላት ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰዱ እንደሚገባም አሳስበዋል።