በጦርነቱ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

4

ባህር ዳር ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) ኤስ ኦ ኤስ ኢትዮጵያ የህጻናት መንደሮች በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍ የሚያስችል የ145 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት አስጀመረ።

የኤስ ኦ ኤስ ህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተር አቶ ሳህለ ማሪያም አበበ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት እንዳሉት ፕሮጀክቱ ለተደራራቢ ሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጥ ነው።

ፕሮጀክቱ በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የተዘጋጀ ሲሆን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ገልፀዋል።


ከ130 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሰረት ተደርጎ የሚተገበር መሆኑን አመልክተዋል።

ኤስ ኦ ኤስ ኢትዮጵያ የህጻናት መንደሮች በክልሉ በርካታ ሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ተወካይ አቶ ጥላሁን አምበሉ ናቸው።

ፕሮጀክቱ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ በጠንካራ ትብብር እንደሚሰራ የጠቀሱት አቶ ጥላሁን ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።