ኢጋድ የትምህርት ጥራት በአካባቢው አገራት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው

4

ሰኔ 2/2014/ኢዜአ/ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ የትምህርት ጥራት በአካባቢው አገራት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት /ኢጋድ/ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ለሚያስተምሩ መምህራን  የሁለት ቀናት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአዲስ አበባ አስጀምሯል።  

በሥልጠናው መርሃ ግብር ከኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ሱዳን የተውጣጡ 45 ሠልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለአንድ ዓመት በሚቆየው የሥልጠና ፕሮጀክት  ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ የተውጣጡ  607 መምህራን ሥልጠናውን አግኝተዋል።

ከኢትዮጵያ 206፣ ከሱዳን 201 እንዲሁም ከኡጋንዳ 200 መምህራን በሁለት ዙር ሥልጠናውን ተከታትለው ማጠናቀቃቸውን ተጠቁሟል።  

ሥልጠናው በዋነኛነት የሥርዓተ-ትምህርት፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ በህይወት ክህሎትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ትኩረት አድርጓል።

ሥልጠናው በቀጣይ በደቡብ ሱዳን፣ በጂቡቲና በኬኒያ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።  

የኢጋድ የጤናና ማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ፈቲያ አልዋን እንደገለጹት ኢጋድ በቀጠናው አገራት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

በተለይም የስደተኛ ልጆች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙና በያሉበት አገር የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲዋሃዱ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የኢጋድ የትምህርት፣ ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ከፍተኛ አስተባባሪ ዶክተር ከበደ ካሳ ናቸው።

በመጠለያ ጣቢያዎች በሥነ-ልቦና ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ሥልጠና በተማሪዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማስመዘግቡንም ነው የገለጹት።