የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለማቋቋም በቂ ዝግጅት እንዲደረግ አሳሰበ

354

ሰኔ2/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ለ20 ሚሊየን ተረጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በጅግጅጋ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በርካታ ዜጎች ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በመላ ሀገሪቱ ካጋጠመው ችግር ጋር ሲነፃፀር እየተከናወነ ያለው የምላሽ አሰጣጥ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ምላሽ ለመስጠትም በዝርዝር በመገምገም በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ  ነው ያሳሰቡት ዶክተር ዲማ።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፤ በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ክልሉ በከፍተኛ የድርቅ አደጋ መመታቱን ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልልም በዘጠኝ ዞኖች ከፍተኛ የድርቅ አደጋ የተከሰተበት መሆኑን ጠቅሰው በአደጋው 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች ተጎጂ ሲሆኑ ከ2 ሚሊየን በላይ የቁም እንስሳትም መሞታቸውን አስታውሰዋል።  

ሆኖም የድርቅ አደጋው ባጋጠማቸው አካባቢዎች የምግብ፣ የውሃ፣ የመድኃኒት እና የእንስሳት መኖ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  

በድጋፍ ሂደቱም የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ረጂ ድርጅቶች፣ ሌሎች ተቋማትና ኢትዮጵያዊያን ከክልሉ ህዝብ ጎን በመሆን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በድርቁ የተጎዱ ወገኖችንም ከመንግስትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የድርቅ ተጎጂዎቸን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያዊያን እና ረጂ ድርጅቶች እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ፤ በድርቅና በጦርነት ለተጎዱ እንዲሁም ከሳዑዲ ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት 60 በመቶውን የተራድኦ ድርጅቶች ደግሞ 40 በመቶ በሚያደርጉት ድጋፍ ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተረጂዎች ቁጥር አንፃር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አንሰተው፤ በድጋፍ አቅርቦት ሂደቱ አሁን ላይ የተራድኦ ድርጅቶች ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ርዳታ አቅራቢዎች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም