በመተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና ሩስያ ወዳጅነት በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል

264

ሰኔ 2/2014/ኢዜአ/ በመተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና ሩስያ ወዳጅነት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የሁለቱ አገሮች ዕውነተኛ ወዳጅነት ሳይደበዝዝ ዘመናትን መሻገሩን ይናገራሉ።

የሩስያና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ከጥንት አስካሁን ክፉ ቀን ያልበገረው በጠንካራ ወዳጅነትና በወንድማማችነት የዘለቀ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በውጭ ሃይሎች ወረራ በተፈጸመባት ጊዜ ሁሉ ሩስያ አጋርነቷን ስለመግለጿ በታሪክ ድርሳናትም ተቀምጧል።

በአድዋ ጦርነትም ሆነ በሁለተኛው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ እንዲሁም በሶማሊያ ወረራ ኢትዮጵያ የሩሲያ ድጋፍ ያልተለያት መሆኑን አምባሳደር ተርኪን ይናገራሉ።

የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ወዳጅነት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለችው የልማት ስራና የሰላም ግንባታ ሂደት የሩስያ ድጋፍ እንደማይለይ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በገጠማት ውስጣዊ ችግር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር ሲሞከር ሩስያ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነቷ መቃወሟንም አውስተዋል።

የሁለቱ አገሮች በመተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተው ወዳጅነት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያን እውነታ በቅጡ የምትረዳው ሩስያ በጸጥታው ምከር ቤት ባላት መቀመጫ ኢትዮጵያን ትደግፋለች ብለዋል።

ከታሪካዊ ልምድ በመቀጠልም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በሰብአዊ መብት ረገድ ካሳየችው ድጋፍ ባሻገር የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል አንዲጠናከር የተቻላትን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከ126 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም