በሶማሌ ክልል የድርቅ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው

69

ሰኔ 2/2014/ኢዜአ/ በሶማሌ ክልል ባጋጠመው የድርቅ አደጋ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በጅግጅጋ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፤  ባለፉት ወራት እንደ ሀገር የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ማጋጠሙን አንስተዋል።

በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሶማሌ ክልል አስከፊ ድርቅ መከሰቱን ጠቅሰው፤ በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 11 ዞኖች ውስጥም ዘጠኙ በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመዋል።

በድርቁ ምክንያትም 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ተጎጂ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

በአሁኑ ወቅትም የድርቅ አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ፣ የውሃ፣ የመድኃኒት እና የእንስሳት መኖ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ስለመሆኑም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም