የአጎራባች ክልሎች ምክክር በሀዋሳ እየተካሄደ ነው

81

ሀዋሳ ሰኔ 2/2014(ኢዜአ) የኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦችና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የአጎራባች የመንግስታት ግንኙነት መድረክ ዛሬ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።

በክልሎቹ  መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በጋራ ለመፍታት፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን በጋራ ማረጋገጥ የመድረኩ ዓላማ ሲሆን በመድረኩ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ይደረግበታል።

በመድረኩ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብን ለመገንባት ይቻል ዘንድ ከተናጠል ጥረቶች የጋራ አቅሞች በተገቢው መንገድ አቀናጅቶና አዋህዶ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል ፎረም ይመሰረታል ተብሎም  ይጠበቃል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባዘጋጀው በዚሁ የምክክር መድረክ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙና የየክልሎቹ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችና ተወካዮች  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም