ፕሮጀክቱ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

69

ሰቆጣ ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) ኤስ.ደብሊው.ኤ.ኤን (SWAN) የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጥምረት ፕሮጀክት በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ከአበርገሌና ፃግብጅ ወረዳዎች ተፈናቅለው በሰቆጣ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች እንደተደረገ የፕሮጀክቱ ተወካይ አቶ አዲሱ ታመነ ገልጸዋል።


በትላንትናው እለት የተደረገው ድጋፍ የ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የብርድ ልብሶች፣ የወለል ምንጣፍ፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሶችና የልብስ ማጠቢያዎች ቁሳቁሶች ናቸው።



ፕሮጀክቱ በመጠለያዎቹ  የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የማብሰያና የንጽህና መጠበቂያ ማዕከላትን እያቋቋመ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ያደረገው ድጋፍ የተፈናቃዮቹን መሰረታዊ ችግር እንደሚያቃልል ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ  የተፈናቃዮቹን የመጠለያ ችግር የሚያቃልሉ ድንኳኖችን  ሰርቶ ማስረከቡን አስታውሰዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ ኪሮስ ሚሰነ ድጋፉ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያለባቸውን ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የተለያዩ ስራዎችን የሚከውኑ አራት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጥምረት እንደሆነም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም