የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስተዋወቀበትን የገርጂ መኖሪያ መንደር ፕሮጀክት ሊያስመርቅ ነው

185

ሰኔ2/2014/ኢዜአ/ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስተዋወቀበትን የገርጂ መኖሪያ መንደር ፕሮጀክት ግንባታን አጠናቆ ሊያስመርቅ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ፕሮጀክቱ አልሙኒዬም ፎርምውርክ ቴክኖሎጂ" የተሰኘ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ያዋለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች ቴክኖሎጂውን በማላመድ ግንባታውን በፍጥነት ያከናወኑበት መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

ቴክኖሎጂው የግንባታ ጥራትና ፍጥነትን የሚያቀላጠፍ እንደሆነም ታውቋል።

ኮርፖሬሽኑ ይህን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በማዋል በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ አስር ወለል ያላቸውን 16 ህንጻዎችን ያየዘ የመኖሪያ መንደር መገንባት ችሏል።

የመኖሪያ መንደሩ ዘመናዊ የደህንነት ጥብቃ ስርዓት የተገጠመለት፣ ከ800 በላይ መኪና ማቆም የሚያስችል ስፍራ፣ የጋራ መጠቀሚያ አዳራሽ፣ የተለያዩ ስፖርት መስሪያ ቦታዎች፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ መናፈሻ፣ አምፊ ትያትር፣ የልጆች መጫወቻንና መዋኛ ገንዳን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

የመኖሪያ መንደሩ ግንባታ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል  እንደፈጠረም የተቋሙ መረጃ ያመላክታል።

የገርጂ መኖሪያ መንደር ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ ያስቻለ፤ ብቃት ያላቸው የመንግስት ፕሮጀክት መሪዎች የታዩበት፤ አሰሪ፣ የግንባታ አማካሪ እና ተቋራጮች  ለአንድ ዓላማ በትብብር በመስራት ትልቅ ነገር እውን ማድረግ  እንደሚችሉ ያሳየ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም የግንባታ ፕሮጀክቱ  ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀመ የከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረትን መፍታት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ በቀበና ሳይት ያስገነባቸውን ሁለት ባለ አስር ወለል ህንጻዎች ግንባታ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ለንግድና መኖሪያ ቤት የሚውሉ ቤቶች ያሉት በ1 ሺህ  167 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ዘመናዊ ህንጻ ግንባታ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም