ከ300ሺህ በላይ ለሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ሶስተኛ ዙር የኮሮና ክትባት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቀቀ

5

አዳማ ሰኔ 2/2014/ኢዜአ/… በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ300ሺህ በላይ ለሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ሶስተኛ ዙር የኮሮና ክትባት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለፀ ።

3ኛ ዙር የኮሮና ክትባት ዘመቻ ስኬታማ ለማድረግ በሞጆ ከተማ አባገዳዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር  ውይይት ተካሄዷል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ግንዶ ለማ ለኢዜአ እንደገለፁት በመጀመሪያና በሁለተኛው ዙር ከ270ሺህ ህዝብ በላይ ክትባቱን መውሰዱን ገልጸዋል።

በዚህም የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ችለናል ያሉት  ሃላፊው በክትባቱ ዙሪያ የሚነዙ አሉባልታዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ክትባቱ በዞኑ 10 የገጠር ወረዳዎች በሚገኙ 294 ቀበሌዎች ላይ ለሶስተኛ ዙር መሰጠት ይጀመራል ያሉት አቶ ግንዶ “በዚህም ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ለመከተብ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የዞኑ የፀጥታ አካላት፣ የጤና ባለሙያዎችና መላው ህብረተሰብ ተገቢውን ድጋፍና ትብብር በማድረግ ዘመቻው በማሳካት የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ክትባቱ ቤት ለቤት የሚሰጥ መሆኑን አውቆ ተገቢውን ትብብር ማድረግ  እንዳለበት ጠይቀዋል።