የቦዲ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ''ኬኤል'' በዓል ሰላምና አንድነት የሚንጸባረቅበት ነው --ጽህፈት ቤቱ

288

ጂንካ ሰኔ 1/2014(ኢዜአ) የቦዲ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ''ኬኤል''በዓል ሰላምና አንድነት የሚንጸባረቅበት ባህላዊ ክዋኔ መሆኑ ተገለጸ።

የቦዲ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ''ኬኤል''በዓል በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ዛሬ መከበር መጀመሩ ተገልጿል ።

የቦዲ ማህበረሰብ በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ በኢትዮጵያ እና የኬንያ አዋሳኝ አካባቢ  ነው የሚኖረው።

የበርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቱውፊቶች ባለቤት የሆነው የቦዲ ማህበረሰብ ራሱን የሚገልፅበት ያልተበረዘ  ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ መሆኑ ተመላክቷል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የሰላማጎ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አረጉ ቻፑላይ ለኢዜአ እንዳሉት የቦዲ ማህበረሰብ ዓመታዊ በዓል ''ኬኤል''  ሰላምና አንድነት የሚንጸባረቅበት ነው።

"ኬኤል" የሚለው ስያሜ የከዋክብት ስብስብና ጥምረት በአንድነት የሚፈጥሩትን ውበት በማየት ለበአሉ ታዳሚዎች የተሰጠ ስያሜ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በየአመቱ በሰኔ ወር መጀመሪያ ቀናት የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል በብሔረሰቡ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በዓሉ ከዘመን መለወጫ ክብረ በዓልነቱ ባሻገር ስለሰላም በጋራ የሚለምኑበት፣ አንድነታቸውን የሚያጸባርቁበት ሁነት መሆኑን አመላክተዋል።

ለውድድሩ የሚዘጋጁ ወጣቶች ወደ  ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት ለአምስት ወራት በደንብ እየተመገቡ እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡

ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ ለመኖር ቃለ መሃላ የሚፈፅሙበት ባህላዊ ስርዓት መሆኑንም አብራርተዋል ።

የባለ ፀግነት ማሳያ የሆነው ''ኬኤል'' የውፍረት ውድድር የበአሉ ድምቀት ከሆኑ ክዋኔዎች አንዱ ሲሆን የትኛው ጎሳ ከብቶቹን በደንብ ተንከባክቧል የሚሉ ነገሮች የሚታይበት ነው ብለዋል ።

"ባሳለፍነው አመት ጠንክሮ በመስራት ሀብት ማፍራት የቻለው የትኛው ጎሳ ነው?" የሚለውን ለመለየትና ጠንክሮ የሰራውን ለማበረታታት፣ያልሰራው ለቀጣይ ጠንክሮ እንዲሰራ ለማነሳሳት የሚካሄድ ውድድር መሆኑ ገልጸዋል።

"በአሉ በአመት አንድ ጊዜ የሚመጣ ትልቅ በአል በመሆኑ በጉጉት ነው የምንጠብቀው " የሚለው ደግሞ የብሔረሰቡ አባል ወጣት ኦይና ጉና ነው።

በበአሉ አከባበር ላይ ስለሰላምና አብሮነት የሚመካከሩበት፣ ቂምና ቁርሾዎች ካሉ በእርቅ የሚፈታበት  ልዩ በዓል መሆኑን ነው የገለጹት ።

የሳላማጎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገልጶክ በበኩላቸው "የቦዲ ብሔረሰብ የመደመር እሳቤን ቀድሞ የተረዳ ማህበረሰብ ነው" ብለዋል።

በበዓሉ ላይ አጎራባች ከሆነው ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚመጡ አርብቶ አደሮች የተሳተፉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከበዓሉ ክዋኔዎች ባሻገር በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮቹ ለጋራ ሰላምና አብሮነታቸው የሚመክሩበት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የበአሉ አከባበር ከሰኔ ወር መጀመሪያ ቀናት ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ እንደሚቆይ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም