በትምህርት ዘርፍ የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማጎልበት የአቅም ግንባታ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው– የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

4

አዳማ፤ ሰኔ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በትምህርት ዘርፍ የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማጎልበት በዕውቀትና ክህሎት እንዲበቁ የአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ መምህራን ጋር በመቀናጀት የሴት አመራሮችና ስራ አስፈፃሚዎች አቅም በዘላቂነት ለመገንባት በሚቻልበት ሂደት ላይ በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል ።

May be an image of 5 people, people sitting and people standing

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ አቶ ስለሺ ታደሰ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ከለውጡ ወዲህ የሴቶች የአመራር ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት አበረታች ቢሆንም በተለይ በትምህርት ዘርፍ በዕውቀትና ክህሎት የታነፁ ብቁና ተወዳዳሪ ሴት አመራሮችን በብዛትና በጥራት ማፍራት አለብን ብለዋል ።

በየደረጃው የሚገጥማቸውን ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግሮችን ለመቅረፍ የሴቶችን አቅም በሁሉም መስክ መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ።

በዚህም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሚና የጎላ መሆኑን የገለፁት ተወካዩ አጫጭርና ረዥም የአቅም ግንባታ ስልጠና በማመቻቸት የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው ማህበሩ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ ለማብቃትና አቅማቸውን ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

May be an image of 1 person, standing and indoor

በተለይ ከዩኒቨርስቲዎችና ማስልጠኛ ማዕከላት ጋር በመተባበር ክህሎትና ዕውቀታቸውን ለማጎልበት እንሰራለን ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የስርዓተ ፆታ ተጠሪ ወይዘሮ ደስታየ ታደሰ እንደሚሉት የሴቶችን ክህሎት፣ ዕውቀትና መልካም ስብዕና በሁሉም ደረጃ ለመገንባት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሴት ተማሪዎች ክበባትን በማደራጀት ከፍተኛ ተግባሮች በመከናነወን ላይ ናቸው።

የፀረ ፆታዊ ጥቃት አደረጃጀቶች እንዲኖሩና ሴቶች ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ የሰላም ዘብ ሆኖ እንዲቆሙ በየትምህርት ቤቶቹ እየሰራን ነው ብለዋል።