በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

4

ሰመራ ሰኔ 1/2014(ኢዜአ) በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረጉት በጂቡቲ ያሉ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲሆኑ ድጋፉንም በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሰመራ ከተማ በመምጣት አስረክበዋል።    

የተወካዮቹ ልዑክ ቡድን ድጋፉን በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ለተቋቋመው ለክልሉ የህዝብ ንቅናቄና ሃብት አሰባሳቢ ኮሜቴ ትናንት አስረክቧል።

የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ዓሊ መሐመድ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት፣ ጅቡቲያዊያን በሽብር ቡድኑ ጥቃት የተፈናቀሉ ወንድሞቻቸውን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የመደገፍ ግዴታ እንዳለባቸው ያምናሉ።

ለእነዚህ ተፈናቃዮች በተለያዩ ጊዜያት የአልባሳትና የምግብ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ሲያረጋግጡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሰባሰበው ይሄው ድጋፍ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

በድጋፉ ቴምር፣ ሩዝና የዳቦ ዱቄትን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦች፣ አልባሳትና ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ የተለያዩ መንቀሳቀሻዎች መካተታቸውንም አመልክተዋል።
አቶ ዓሊ እንዳሉት የተጀመረው ድጋፍ ተፈናቃዮች ወደ መደበኛ ኑሯቸው እስከሚመለሱ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ድጋፉን በህግ ማስከበር ዘመቻው የተቋቋማው ክልላዊ የህዝብ ንቅናቄና ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ መሐመድ ደርሳ ናቸው የተረከቡት።

በዚህ ወቅትም ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በክፉም ሆነ በደጉ የቆየ የመረዳዳትና መደጋገፍ አኩሪ ባህል እንዳላቸው ተናግረዋል አቶ መሐመድ።

“ዛሬ የተደረገው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፍም ይህንኑ አኩሪ እሴት የሚያስቀጥል ነው” ብለዋል።
በተለያዩ አካላት የሚደረገው ድጋፍ መንግስት ለተፈናቀሉ ወገኖች እያደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ ለተጎጂዎች የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።
ድጋፉን ላደረጉት የጅቡቲ ወጣቶች፣ ሴቶች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተጎጂዎች ስም ምስጋናቸውን ገልጸው፣ ሌሎች አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።