የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት አዳዲስ ባንኮች ፈቃድ ሰጠ

422

ሰኔ 1/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት አዳዲስ ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳሬክተር ፍሬዘር አያሌው፤ በፋይናንስ ዘርፉ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ለውጦችን ተከትሎ በርካታ ባንኮች የመመስረቻ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ባንክ ለመመስረት የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የካፒል መጠንን ከ500 ሚሊዮን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉን አስታውሰው አጠቃላይ መስፈርቱን ላሟሉ ፈቃድ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ መሰረት የመመስረቻ ፈቃድ ከጠየቁ 25 አዳዲስ ባንኮች መካከል ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ 8 ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል።

በብሄራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኙ ስምንት ባንኮች በተጨማሪ 3 ባንኮች ፈቃድ የማግኘት ሂደቱን እያጠናቀቁ ሲሆን ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውሰጥ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

በብሔራዊ ባንክ ከቅድመ ማመልከቻ ሂደት ጀምሮ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸው    የምስርታ ሂደቱ ካልተሳካ ለባለአክሲዮኖች ገንዘባቸው ተመላሽ ይሆናል ብለዋል።

በተመሳሳይ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ በ2012 አ.ም ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሰረት መስፈርቱን ያሟሉ 3 አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ሁለት አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ደግሞ መስፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።

የባንክ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ከ120 ሺህ በላይ ዜጎች ቀጥተኛ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን አዳዲስ ባንኮች ወደ ዘርፉ መምጣታቸው አማራጭ አገልግሎትን ከማቅረብና የስራ እድል ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ለ28 ባንኮች ፈቃድ መስጠቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም