በተለያዩ አደጋዎች ችግር ለገጠማቸው ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

102

ሰኔ 1/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ችግር ለገጠማቸው ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገለጹ።

ኮሚሽኑ የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በጅግጅጋ ውይይት አካሂዷል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በሚያጋጥሙ ችግሮች ለተጎጂዎችና ተፈናቃይ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት በአፋር፣ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች በጦርነት እንዲሁም በደቡብ፣ ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የተጠናከረ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው ጋር የተደረገው ውይይትም በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ እየተደረገ ያለውን ስኬት የበለጠ ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለመሙላት ግብዓት የሚገኝበት መሆኑን ገልጸዋል።  

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፤ ባለፉት ወራት እንደ ሀገር የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ፈታኝ እንደነበሩ ገልጸዋል።    

የሶማሌ ክልልም በዘጠኝ ዞኖች ከፍተኛ የድርቅ አደጋ የተከሰተባቸው መሆኑን ጠቅሰው በአደጋው 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች ተጎጂ ሲሆኑ ከ2 ሚሊየን በላይ የቁም እንስሳትም መሞታቸውን አስታውሰዋል።  

ሆኖም የድርቅ አደጋው ባጋጠማቸው አካባቢዎች የምግብ፣ የውሃ፣ የመድኃኒት እና የእንስሳት መኖ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  

በድጋፍ ሂደቱም የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ረጂ ድርጅቶች፣ ሌሎች ተቋማትና ኢትዮጵያዊያን ከክልሉ ህዝብ ጎን በመሆን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በድርቁ የተጎዱ ወገኖችንም ከመንግስትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የድርቅ ተጎጂዎቸን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያዊያን እና ረጂ ድርጅቶች እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም