በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ፈተና እንዳይገጥመው ህዝቡ ለፍቅርና ለይቅርታ ቦታ ሊሰጥ ይገባል- የሐይማኖት አባቶች

824

አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ፈተና እንዳይገጥመው ህዝቡ ለፍቅርና ለይቅርታ ቦታ መስጠት እንዳለበት የሐይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ቡራኬ በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ፈተና እንዳይገጥመው ህዝቡ ለፍቅርና ለይቅርታ ቦታ መስጠት አለበት።

ኢትዮጵያ የቀደመ ደማቅ ገናናነቷን መልሶ ለማረጋገጥ ሲሉ ውድ ልጆቿ ለለውጥ ጥረት ሲያደርጉ ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ መቆጠራቸውን ጠቅሰው የተደረጉት የለውጥ ጥረቶች የሚፈለገው ደረጃ ላይ ሳይደርስ ነገሮች እየተወሳሰቡ ከለውጡ ይልቅ ጥፋት እየቀደመ ፈተና ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

መቃቃርን፣ ጥላቻንና ግጭትን የሚያስከትሉ ኃይለ ቃላትን መለዋወጥ በዜጎች መካከል ዋጋ የሚያስከፍል ስለሆነ በአዲሱ ዓመት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወገዱ ይገባል ብለዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው በሰላማዊ መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እንዲሁም ምሁራን፣ የጥበብ ባለሙያዎችና ወጣቶች የቃላት ውርወራን አቁመው በፍቅርና በይቅርታ ለአገር አንድነት መስበክ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ህዝቦች በመፈቃቀርና በመዋደድ ስለሰላምና አንድነት የበለጠ የሚሰሩበት ዓመት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

”በዓሉን ስናከብር ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በችግር ላይ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የአልጋ ቁራኛና ለተፈናቀሉ ወገኖች በመለገስ አብረናቸው ልናከብር ይገባል” ብለዋል።

ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ በየትኛውም አካባቢ የመኖርና የመስራት መብቱ ተከብሮለት እንዲንቀሳቀስ ወጣቱ ለሰላምና ለፍቅር ዋጋ እንዲሰጥ  አሳስበዋል።

የእምነት ተቋማት ለምዕመናን መሠረታዊ የሆነውን የፈጣሪን አስተምህሮ ተጠቅመው ስለ ሰው ልጅ ደህንነት፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር እና ስለአብሮ መኖር በማስተማር የሰዎችን ህሊና ማነጽ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በአዲሱ ዓመት ባለፉት ጊዜያት የተገኙ መልካም ልምዶችን በማጠናከር እና የታዩ ችግሮችን በማረም ከዘመኑ ጋር በማስማማት ልናስቀጥላቸው ይገባል ብሏል።

“በ2010 ዓ.ም በአገሪቱ በጎና በጎ ያልሆኑ በርካታ ክንውኖች ተመልክተናል” ያለው ጉባዔው የአገሪቱ መልካም እሴት የሚያጎድፉ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የማይገልጹ አመለካከቶችና ተግባራትን እንዲስተካከሉና እንዲታረሙ አሳስቧል።

”ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ችግሮችና በደሎች በምህረት፣ በይቅርታና በፍትህ ለመደምደም በአካባቢና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚፈለግብንን ሐይማኖታዊና አገራዊ ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል” ብሏል።

በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ብሔርንና  እምነትንም መሠረት ያደረጉ ጥላቻዎችን በማውገዝ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጉባዔው ጠይቋል።

በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጎልቶ የታየው የመረዳዳትና የመደጋገፍ እንቅስቃሴም በሁሉም የሐይማኖት አስተምህሮ የሚወደድና የሚደገፍ ነው ያለው መግለጫው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

በመጨረሻም የተጀመረው ለውጥ ሂደት እንዲጠናከርና አገሪቱ ከድህነት ተላቃ የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ያሳሰበው ጉባዔው አዲሱ ዓመት የጤና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነትና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።