ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴት መሠረት አድርጎ ሊካሄድ ይገባል - ምሁራን

108

ጎባ ግንቦት 30/2014(ኢዜአ)  ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴት መሠረት አድርጎ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር መደላድል ይፈጥራል ሲሉም ምሁራኑ ገልጸዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ወቅት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመለየትና ለውይይት በማቅረብ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ በማወያየት መግባባት ላይ ለመድረስ ሊሰራበት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ህዝቡን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመምራት በተለይም በአገር በቀል እውቀትና በሳይንሱም ጭምር  በመሞገት ማሳመን ደግሞ ከምሁራኑ የሚጠበቅ በመሆኑ በዚህም ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩን በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ምሁራን መካከል የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሌንጮ ሳሙኤል እንዳሉት በቀጣይ በአገሪቱ ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሁሉንም የህረተሰብ ክፍል ባካተተ መልኩ የሚካሄድ ከሆነ ለሀገራዊ መግባባቱ መፈጠር በር ይከፍታል፡፡

አገራዊ መግባባት ማለት በአገሪቱ ከዚህ በፊት በተፈጠሩና አሁናዊ ሁኔታዎች ላይና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ፋይዳው የጎላ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ አገሪቱ የቆየና ሰፊ አገር በቀል እውቀቶችና ባህሎች ስላሏት ያንን አውጥቶ ለምክክሩ በተግባር ማዋል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንመ ጠቅሰዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥም ሆነ በዘርፉ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና ትርክቶች ዙሪያ ምርምር በማድረግ ለስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡

የምክክር መድረኩ የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበትና አሳታፊ ሊሆን እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ጉሚ ቦሩ ናቸው፡፡

በተለይ ምሁራን ዜጎች ድምጾቻቸውን በመድረኩ አሰምተው ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህርና በህብረተሰቡ ማህበራዊ ችግሮች ላይ ምርምር እንደሚያካሄድ ግለሰብ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ እንዲሳካ  የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ተቀራርቦ በመነጋገር ቂምና ቁርሾ እንዲሁም ከፋፋይ ትርክቶችና አስተሳሰቦችን በማስወገድ አገራዊ አንድነት ማምጣት የሚያስችል መድረክ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ መሐመድ አሚን ናቸው፡፡

በአገሪቱ አብዛኛውን ጊዜ ህብረተሰቡን ለመከፋፈልና የልዩነት ምንጭ ተደርጎ እየተሰራበት ያለው ችግሮች ምንጫቸው መሰረተ ቢስ ትርክት ነው ይላሉ አቶ ሁሴን።

ህብረተሰቡ ችግሮቹን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት የልዩነት ምንጭ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ጉዳዮች ዙሪያ በመመካከር ከመግባባት ላይ መድረስ የሚያስችሉት በርካታ ባህሎችና ወጎች ስላሏቸው ያንን መጠቀም ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል የተባለውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 ማጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም