በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም አዲስ ዓመት ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ነው- አምባሳደር ማይክል ሬይነር

1973

አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም  አዲስ ዓመት ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ገለጹ ።

አምባሳደሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም  አዲስ ዓመት ለራሳችን፤ ለቤተሰቦቻችን  እንዲሁም ለጓደኞቻችን  ብሩህ ተስፋን የሰነቀ እንደሆና “በኢትዮጵያ ከቀደሙት ዓመታት ይልቅ ዘንድሮ ይበልጥ ለምልሞ የሚታይ” እንደሆነ መግለጻቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በአገራቸው እየታየ ባለው አዲስ ራዕይ የተደመሙ ኢትዮጵያውያን፤  በለውጡ ሰላማዊ፣ አካታች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን  እንደሚያልሙም ተናግረዋል።

አምባሳደር ማይክል ሬይነር አዲስ ዓመት ሲያስቡ ኢትዮጵያውያንና መንግሥታቸው ለለውጡ ያሳዩት ቁርጠኝነት እንደሚያስታውሳቸውና ቁርጠኝነቱ በውስጣቸው የሚመላለሰውን ዓይነት ጥንካሬ፤ ተስፋ እና አዎንታዊነትን የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል።

አዲስ ዓመት ታላቅ ተስፋ እና እድልን ይዞ ቢመጣም፤ ስለቀጣይነቱ ምንም ዓይነት ዋስትና እንደማይሰጥና የተሻለ ነገን መገንባት ከተስፋ በላይ የሆነ ሥራን እንደሚጠይቅም አመልክተዋል፤ መላው ኢትዮጵያዊ ጠንክሮ መስራት እንዳለበትም በማሳሰብ።

ህልማችን፤ መጪው ጊዜ  ለኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት የተሻለ  እንዲሆን ከሆነ፤  ሁላችንም የድርሻችንን መወጣትና ግልጽ፤ ገንቢ አንዳንዴም አስቸጋሪ ውይይቶችን ማካሄድ ያስፈልግናልም ብለዋል።

ሰዎች ተመሳሳይ ግብ  ቢኖራቸው እንኳ፤ ወደ ስኬት የሚያደርሳቸው የየራሳቸው የተለያየ ሀሳብ እንደሚኖራቸው መቀበል እንደሚያስፈልግና በተመሳሳይም ከአንድነት ይልቅ በሰዎች መካከል ክፍፍልን ከሚጋብዙ እና በተሳሳተ መንገድ አመጽን ከሚያበረታቱ ሀሳቦች በተቃራኒ መቆም እንደሚገባ ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

እንዲሁ ስለ ተግዳሮቶች ከማውራት ይልቅ ብዙ መሥራት እንደሚገባና “ትኩረታችንን መፍትሔ ማፈላለግ ላይ ማድረግ” እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የምንፈልገውን አዎንታዊ ለውጥ እውን ለማድረግ፤ እያንዳንዳችን የየድርሻችንን መወጣት አለብን የሚለውን ሀሳብ በደንብ መቀበልም እንደሚገባ አስታውቀዋል።

“በአሜሪካ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ ቃል የምንገባበት ባህል አለን” ያሉት አምባሳደር ማይክ እኩለ ሌሊት ላይ ከአሮጌው ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገራችን ሲበሰር፤ ሁሉም የአሜሪካ ዜጋ ለራሱ በዓመቱ የተሻለ ነገር ለመከወን ቃል እንደሚገቡ አስረድተዋል።

ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ለመከተል፤ አዲስ ክህሎት ወይም ለሌሎች መልካም ነገርን ለመዋልና የምንመኘውን የተሻለ ነገ ለማሰብም ሆነ በጥረታችን እውን ለማድረግ የአዲስ ዓመት ቃልኪዳን ትልቅ እድልን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን ሲቀበሉ፤ የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ለመቀየር የሚያስችል ጥረት ለማድረግ ቃል እንዲገቡም አምባሳደሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በጋራ ለተሻለ ነገ የሚሰራ ከሆነ ከአምናው ዘንድሮ በእርግጠኝነት የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ቀጣይ ስኬት እና ለሁለቱ ሀገራት የበለጠ ጠንካራ አጋርነት የበኩሉን ለመወጣት ትልቅ ፍላጎትና ዝግጁነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚገባቸውን የተሻለ ነገ ለመፍጠር፤ ኢትዮጵያውያን እየተወጣችሁ ያላችሁትን ነገር ለመስማት ዝግጁ ነኝ ብለዋል አምባሳደር ማይክል።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ህዝብ  የሰላም፤ የብልፅግና እና የደስታ እንዲሆን ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል።