ወልዲያ ሆስፒታል ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው

2

ወልዲያ ግንቦት 30 /2014 (ኢዜአ) የወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከዘጠኝ መቶ ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

ሆስፒታሉ ሕክምናውን እየሰጠ ያለው “ሂማልያን ካታራክት” ፕሮጀክት ከተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑንም ገልጿል።  

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ የኋላው እንዳሉት፣ ሆስፒታሉ የአሸባሪው ህወሓት ወረራን ተከትሎ ከደረሰበት ዝርፊያና ውድመት አገግሞ ለህብረተሰቡ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።

በአካባቢው በሰዎች ላይ በስፋት የሚስተዋለውን የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቀዶ ሕክምና ለማስተካከል የሕሙማን ልየታ ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም ገልፀዋል።

ሕክምናው ከግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑን ተናግረዋል።  

አቶ ፍሰሀ እንዳሉት በነጻ ሕክምናው 800 ሰዎችን ለማስተናገድ ቢታቀድም የሕሙማን ቁጥር በመጨመሩ 960 ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ትናንት በመጀመሪያው እለት በተደረገው ህክምና ብቻ 196 ሰዎችን በማከም የዓይን ብርሃናቸውን ለመመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

”የሂማሊያን ካታራክት” ፕሮጀክት አስተባባሪ ሲስተር መሰረት ፋንታሁን በበኩላችው፣ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ማየት ያልቻሉ ወገኖችን ብርሃናቸውን በቀዶ ሕክምና ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“ሕክምናውን የሚያገኙ ወገኖች ከተለያዩ የሰሜን ወሎ ዞን ወረዳዎች የመጡ በመሆኑ የትራንስፖርት፣ የሕክምናና የምግብ አገልግሎቶችን በነጻ እንዲያገኙ ተደርጓል” ብለዋል።

ለታካሚዎቹ ለአንድ ወር የሚያገለግል መድሃኒት አብሮ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም በየአካባቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋማት በኩል የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሕክምና አገልግሎቱን ካገኙት መካከል የ65 ዓመቱ የመቄት ወረዳ ነዋሪ ሸህ ወርቁ ሙሄ ”ላለፉት 3 ዓመታት ሁለቱም አይቼ ማየት ባለመቻላቸው ከምወደው የእርሻ ሥራ በመራቅ በሰው እጅ ወድቄ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ በተደረገላቸው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና የዓይን ብርሃናቸው ተመልሶ ዳግም ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የማየት አቅማቸው እየቀነሰ በመምጣቱ ከቤት መዋላቸውን የተናገሩት ደግሞ የአንጎት ወረዳ ነዋሪ አቶ ወዳጅ ይርዳው ናቸው።

ከህክምናው በፊት ባጋጠማቸው የአይን ብረሃን ችግር የእርሻ ሥራቸውንም ሆነ ሌሎች ተግባራትን በራሳቸው ማከናወን ባለመቻላቸው ይቆጩ እንደነበርና በተደረገላቸው የሕክምና  ብረሃናቸውን  መልሰው በማግኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል።