በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ከ87 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ነክ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ተልኳል

112


ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ከ87 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ነክ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል መላኩን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጪ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግይ ክልል እንዲገባ የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ መሆኑንም ሃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በሚያዚያና ግንቦት ወር ብቻ ከ1 ሺህ 300 በላይ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን አንስተው፤ይህም በአውሮፕላን ከሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተያዘው በጀት አመት ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ ከ87 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ነክ ድጋፍ ወደ ስፍራው መላኩንም ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

130 ሺህ ኪሎ ግራም ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ እንዲሁም 783 ሺህ ሊትር ነዳጅም ወደ ክልሉ መግባቱን እንዲሁ፡፡

በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ለሚኖሩ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ መንግስት የተኩስ አቁም ያደረገ ቢሆንም አሸባሪው ህወሃት ከዚህ በተቃራኒ ጦርነት ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ሕወሓት በዚህ የእርሻ ወቅት ችግር የሚፈጥር ከሆነ ቅድሚያ ተጎጂ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊዋ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ጉዳይ በተገቢው መልኩ ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በመደገፍ ረገድም መንግስት ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስረድተዋል።

በዘላቂነት የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም መንግስት የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ተቋማዊ አሰራሮችን ማዘጋጀትና ስብዓዊ ድጋፎችን የሚያደርግበትን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲሁም የኩታ ገጠም እርሻና የመስኖ ልማት ስራዎችም ይህንኑ ችግር ለመቋቋም እንዲረዱ የታለሙ ናቸው ብለዋል።

ዘንድሮ ባጋጠመው ድርቅ ምክንያትም 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አነሳሽነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ሶስት ዓመታት በአጠቃላይ ከ18 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል መቻሉን ተናግርዋል።

በመርሃ ግብሩ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ውጥን ያለ ሲሆን፤ የዘንድሮው ዓመት ደግሞ የመርሃ ግብሩ የመጨረሻ ምእራፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


የዘንድሮው መርሃ-ግብርም በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጀመራል ነው ያሉት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ከከተማ ግብርና እና ከጓሮ አትክልት ልማት ጋር ተቀናጅቶ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም