የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ስርዓቱን የማዘመን ሥራ እየተሰራ ነው - ሚኒስቴሩ

381

ሀዋሳ ግንቦት 30/2014(ኢዜአ) የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ስርዓቱን ማዘመን በዘርፉ የሚታየውን ኢፍትሃዊ አሰራር በማስቀረት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ስራውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘርፉን ለማዘመን የጀመረው ስራ እንዲሳካ የአመራሩንና የባለሙያዎች ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጀን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ ያለውን መሬት በፍትሃዊነት ለመጠቀም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመሬት ምዝገባ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።

የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና የመረጃ ስርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ ደግሞ በዘርፉ ያሉ ኢፍትሃዊ አሰራርን በማስቀረት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የምዝገባ ሂደቱ እያንዳንዱ ሰው በቂ መረጃ እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ስራው እንደ ሀገር ከተጀመረ ዓመታት መቆጠራቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው ሀገራዊ አለመረጋጋት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥራው በአግባቡ እንዳይከናወን ማነቆ እንደነበሩ አስታውሰው፣ ዘንድሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ሀዋሳን ጨምሮ በሲዳማ ክልል ባሉ ከተሞች እየተሰራ ያለውን ሥራ ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንደ ሀገር 6 ሚሊዮን የከተማ መሬት ይዞታ መኖሩን የገለጹት አቶ ፋንታ፣ ከዚህ ውስጥ የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው 12 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን ልጸዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት ሂደት በየዘርፉ የተሰሩ በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የከተማ መሬት ምዝገባና መረጃ ኤጄንሲ የምዝገባ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ባይብኝ በበኩላቸው፣ ስርዓቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዘርፉ የባለሙያ እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል።

በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ዘመናዊ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና ማረጋገጫ ሥራ ስኬታማ እንዲሆን የዘርፉ ተቋማትን ቅንጅታዊ ስራና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በእስካሁኑ ሥራ አፈጻጸሙ እንደ ሀገር ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ "ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተቀመጠ አቅጣጫ ሥራዎችን በፍጥነት ለመጨረስ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ምክትል መምሪያ ሃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ በከተማው ባለፉት ዓመታት ከ12 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ5 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታ መረጋገጡን ጠቅሰው፣ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ስራው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

የከተማውን መሬት ይዞታ በዘመናዊ መልክ መመዝገብና ማደራጀት የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

የተጀመረው ሥራ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅም አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር ጭምር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ታሪኩ አስረድተዋል።

እንደ ሀገር በመጪው አሥር ዓመታት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመሬታ ይዞታን ለማረጋገጥ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም