የከተማ አስተዳደሩ ችግር ፈቺ ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

6

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ የከተማ አስተዳደሩ ችግር ፈቺ ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ 12ኛዉ የቴክኒክ ሙያና ቴክኖሎጂ ሳምንት አውደ-ርዕይ ተከፍቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግሥት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ሥራዎች ለውጥ ለማምጣት ትኩረት አድርጓል ብለዋል።  

ይህንንም ተከትሎ በተለይም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተደራሽነታቸውን የማስፋትና አሰራሮችን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

የሥራ አካባቢያቸውን ምቹ  ማድረግና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራም መሠራቱን ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የውጭ ምንዛሪን የሚያስቀሩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ መደረጉንም ገልጸዋል።

በዚህም ተቋማቱ ውጤታማ ሥራ በመሥራት የዜጎችን ችግር መፍታት መጀመራቸውን ነው የጠቆሙት።  

ከተማ አስተዳደሩም በቴክኖሎጂ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማብቃት ሃሳብ እንዲያፈልቁና የፈጠራ ውጤቱን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።  

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው፤ “ክህሎት በራስ የመተማመን ምንጭ ነው” ብለዋል።

በራስ መተማመን የሰው ልጅ ነጻነት አንድ አምድ ሲሆን ነጻነት የፈጠራና የብልሃት መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።

“በአውደ-ርዕዩ ላይ የቀረቡት የፈጠራ ሥራዎችም የችግሮቻችን ማሸነፊያ መሳሪያዎች ክህሎት መሆኑን ማሳያ ነው” ብለዋል።

“ክህሎትን አጠናክረን በገነባን ቁጥር የአገሪቱ የመፍጠርና የማድረግ አቅም የመገንባት እድላችንን በማስፋት የምንፈልገውን ብልጽግና ለማረጋገጥ ያስችለናል” ሱሉም ተናግረዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት በወዳጅነት አደባባይ በሚካሄደው አውደ-ርዕይ አንድ የምርታማነት ማሻሻያ የልህቀት ማዕከልና 14 ኮሌጆች ተሳታፊ ሆነዋል።