በኢትዮጵያ መጠነ-ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸው በኢኮኖሚው ላይ ሊከሰት የሚችለውን ከፍተኛ ጫና ያስቀረ ነው

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸው በኢኮኖሚው ላይ ሊከሰት የሚችለውን ከፍተኛ ጫና ያስቀረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ አመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባው በፌዴራል መንግስት የ2015 ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት አድርጓል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፤ የፌዴራል መንግስት የበጀት አመቱ ረቂቅ በጀት ዙሪያ ለምክር ቤት አባላት ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ረቂቅ በጀቱ አገራዊ የኢኮኖሚ ደረጃውን፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያን፣ የመንግስትን ወጪና ገቢ አቅጣጫዎችና የበጀት ድልድሉን ታሳቢ ማድረጉን አስረድተዋል።  

የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የፋንናንስ፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች እንዲሁም መዋቅራዊና የዘርፍ ማሻሻያዎች ታሳቢ መደረጋቸውንም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የተዛባውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን ለማስተካከል ይረዳል ተብሎ የታመነበትን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መንግስት በተጠናከረ መንገድ ተግባራዊ ስለማድረጉም አንስተዋል።

በኢኮኖሚው መልካም ለውጦች መታየት የጀመሩ ቢሆንም ከ2012 በጀት አመት አጋማሽ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በማጋጠማቸው የማሻሻያዎቹ ትግበራ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን አስረድተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ የአምበጣ መንጋ፣ ድርቅና የጎርፍ አደጋ፣ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል  የነበረው ጦርነትና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም እስካሁንም የዘለቀው የራሺያና ዩክሬን ጦርነት ከፈተናዎቹ መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመሆኑም በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዝርዝር መመልከቱ ለ2015 በጀት ዓመት ያለውን እድምታ ለመረዳት ያስችላል ብለዋል።

የዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2013 በጀት አመት ወደ 1ሺ 92 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።

ባለፉት 2 አመታት የበርካታ የዓለም ሀገራት ኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ሲሆን ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሀገራት ከዜሮ በታች እድገት አስመዝገበዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት ተግባራዊ የተደረጉት መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተከሰቱትን ተጽእኖዎች ለመቋቋም አቅም የፈጠረ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም