የህግ ማስከበር ተግባሩ ያለስጋት ወደ ልማት ተግባራችን እንድንሰማራ እድል ፈጥሮልናል- አርሶ አደሮች

3

ባህር ዳር ግንቦት 30/2014 (ኢዜአ) መንግስት በህገወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ እየወሰደ ባለው ህግ የማስከበር ስራ ያለምንም ስጋት ወደልማት ስራቸው እንዲሰማሩ እድል እንደፈጠረላቸው በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የዚገም ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በብሄረሰብ አስተዳደር ዞኑ በዚገም ወረዳ “ቅላጅ” ከተማ “ሰላማችን ለሁላችን ” በሚል መሪ ቃል የህግ ማስከበር እርምጃው ላይ ያተኮረ ከንፍረንስ ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉት አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት የአርሶ አደሩን ንብረት በመቀማትና በመዝረፍ ከፍተኛ በደል ሲያደርሱ ቆይተዋል።

የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር በላይ ዘለቀ እንዳሉት መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃውን መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ከቤቱ ወጥቶ በነጻነት የመንቀሳቀስ እድል እንዳልነበር ተናግረዋል።

ህገወጦች በሚፈጽሙት ወንጀል ምክንያት ወደ ገበያ ሄዶ በሰላም የመመለስ፣ልጆችን የማስተማርና እንስሳትን ወደመስክ የማሰማራት ተግባራት ጭምር ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በሰላም ወጥቶ ወደ ልማት ስራው ከመሰማራት ይልቅ እራሱንና ቤተሰቡን ከጥቃት ለመከላከል እንቅስቃሴውን እንዲገድብ ተገዶ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን በመንግስት እየተወሰደ ባለው ህግ የማስከበር ስራ ሰላም እየሰፈነ በመሆኑ ወደ ልማት ስራ እየተመለሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው ህገ-ወጦች በማን አለብኝነት በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ በደል ሲያደርሱ መቆየታቸውን የሚገልጹት ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ስንታየሁ መኮንን ናቸው ።

በህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች የአርሶ አደሩን ንብረት ከመዝረፍ ባለፈ የልማት እንቅስቃሴዎችን  ሲያደናቅፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ህግ የማስከበር ስራ መጀመሩ የሚደገፍና ዘላቂነት ሊኖረው የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ አሁን የተገኘው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በህግ-ማስከበር ዘመቻው የተደራጀ ዝርፊያ ፣ ግድያ፣የመሬት ወረራ፣ኮንትሮባንድ ንግድና ማጭበርበር ድርጊቶችን የሚፈጽሙ በርካታ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

አርሶ አደሩን የእርሻ በሬ ሳይቀር በመዝረፍ ህይወቱ እንዲመሰቃቀል የማድረግና  ህብረተሰቡ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ  በስጋት ውስጥ እንዲቆይ ተደርጎ ነበር ብለዋል።

መንግስት በጀመረው የህግ-ማስከበር ዘመቻ በየደረጃው ያለ አመራርና የፀጥታ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር  ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በህግ ማስከበር ዘመቻውም በዞኑ 172 ነፍሰ ገዳዮችን ጨምሮ 1ሺህ 392 ወንጀለኞችን ወደ ህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

ከነፍሰ ገዳዮች ውስጥም  118ቱ በዚገም ወረዳ የሚገኙ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ህግ-የማስከበር ስራው ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ገልጸዋል።

በሰላም ከንፍረንሱ የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተጋባዥ  የመተከል ዞን አመራሮች ተገኝተዋል።