የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አመለካከትን ዜጎች በጋራ ሊታገሉ ይገባል - ምሁራን

154

ሆሳዕና ግንቦት 30/2014 (ኢዜአ) .... ዜጎች ለብዝሃ ባህል ፈተና የሚሆኑ እንደ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ያሉ አመለካከቶችና ድርጊቶችን በተደራጀ መልኩ ሊታገሉ እንደሚገባ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጽንፈኝነት በባህሪው ግለኝነትን የሚያበረታታ በመሆኑ ለማንም የማይበጅና ለብዝሃ ባህላችንም ፈተናን የሚደቅን ነው ይላሉ።

ይህን ለልማታችን ማነቆ የሚሆነውን አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ሁሉም ዜጋ ሊታገለው ይገባል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መሐመድ አዎል ጽንፈኝነት አንድ ሰው  ብቻውን ትክክል ሌላውን ስህተት አድርጎ የመመልከት የጅምላ ፍረጃ እይታ መሆኑን ያስረዳሉ።

በዚህም የመረጡት ሃይማኖት ብሄር ወይም ሌላ ነገር ቢሆን በሌሎች ላይ በሃይል ተፅዕኖ በመፍጠር ግባቸውን ለማሳካት የሚፈጸም ድርጊት በመሆኑ ልንታገለው ይገባል ሲሉ  ተናግረዋል።

በጥቅሉ የአክራሪነትና የፅንፈኝነት አስተሳሰብ ራስ ወዳድነትን በማጎልበት ለሌሎች ግድየለሽነትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለዘመናት ብዝሃነትን አቅፋ የያዘችና ለብዙ ሀገራት ተምሳሌት ሆና መኖሯን ጠቅሰው አሁን ዘመን አመጣሽ አኗኗሮችን ተከትለን የእኛ የእነርሱ የሚል ነገር መፍጠርና መከተል በፍጹም ተገቢነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

አክራሪነት እና ጽንፈኝነት ከአገርና ከአካባቢም አውርዶ በሰፈር በቀበሌ መታጠርን የሚያስከትል በመሆኑ ለብዝሃነትና ለአብሮነት የማይበጅ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽንፈኝነት ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የማስፋት አጀንዳ ያለው ዕይታ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊና የፌዴራሊዝምና የአካባቢ መንግስት ትምህርት መምህር አባስ ሉባኔ ናቸው።

ለአንድ ብሄር ወይም ሃይማኖት ወገንተኛና ተቆርቋሪ በመምሰል ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ዋና መገለጫቸው መሆኑን ያነሱት መምህር አባስ፤ በእውነቱ ግን ለግል ጥቅም እንጂ ለብሔሩ እውነተኛ ተቆርቋሪ አይደሉም ብለዋል።

የእነዚህ አካላት መሰረታዊ ዓላማ የሀገሪቱን ለዉጥና እድገት  ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን በተለያየ መንገድ ግርግር ይሁን ግጭት በመፍጠር የግል ጥቅማቸዉን ማስጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ግባቸውን ለማሳካት የተለያዩ ጸብ ቀስቃሰሽ አማራጭ እንደሚከተሉ ገልጸው ኢትዮጵያዊያን መንቃትና የተለየ ነገር ስንመለከት ለምን ብለን መጠየቅ ይገባናል ብለዋል።

ምሁራን ደግሞ በተለያየ መልኩ የቀሰሙትን ዕውቀት ተጠቅመው የታሰበው ሁለንተናዊ ብልጽግና ግብ እንዲመታ በሰላም ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከማንኛውም ፅንፈኛ አስተሳሰብና አመለካከት ገለልተኛ በመሆን እያበበ እየመጣ ያለውን ኢትዮጵያዊነት እንዲጎመራ በምንችለው ሁሉ ማገዝ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን ሲሉም አሳስበዋል።

የጽንፈኝነት እይታ ለማንም የማይበጅ መሆኑን የጠቀሱት መምህሩ፤ በተለይ ከአብሮነትና የመቻቻል ባህላችን ያፈነገጡ አተያዮችን መጋፈጥና እንዲስተካከሉ ሁሉም ዜጋ በያለበት መታገል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም