ድርጅቱ ለአፋር ተፈናቃዮች የ7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

3

ሰመራ ግንቦት 30/2014 (ኢዜአ) የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት በአፋር ክልል በህወሃት ሽብር ቡድን ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ሰጠ።

ድጋፉን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለአፋር ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ በሰመራ አስረክበዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደተናገሩት የአፋር ሕዝብ አሸባሪው ቡድን የሠላምና ደህንነት አደጋ በደቀነበት ወቅት በጀግንነት በመመከት አኩሪ ታሪክ ሰርቷል።

በተለይም የሀገሪቱ ገቢና ወጪ የትራንስፖርት መሥመርን ለማስተጓጎል ያደረገውን ሙከራ ማክሸፉ ትውልድ ሲያወሳው እንደሚኖር ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ የሀገር ህልውናን ለማስቀጠል ባደረገው እንቅስቃሴ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ኢትዮጵያውያን በአብሮነትና በመረዳዳት ባህላችን መደገፍ አለብን ብለዋል።

ድርጅታቸው ለተፈናቃዮቹ አምስት ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብና ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ ድጋፎችን ማድረጉን ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በክልሉ በቆየበት ወቅት ካደረሰው ጉዳት መልሶ ለማቋቋም የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው።

ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በክልሉበጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ከእለት ደራሽ ሰብአዊ እርዳታ ጀምሮ እስከ መልሶ ማቋቋም ድረስ ድጋፉ  እንዲቀጥል ጠይቀዋል።