በክልሉ ከ80ሺ በላይ ዜጎችን የኮቪድ- 19 ክትባት ተጠቃሚ ለማድረግ ከነገ ጀምሮ በዘመቻ ይሰራል--የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ

195

ሀረር ግንቦት 30/2014 (ኢዜአ) በሀረሪ ክልል ከነገ ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ ከ80ሺ በላይ ዜጎችን የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንዲወስዱ እንደሚሰራ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ፡፡

ክትባቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭቱን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቆጣጠር ሚናው የጎላ መሆኑን ተገልጿል፡፡

የቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሀረሪ ክልል 80 ሺህ አንድ መቶ  ሰዎች  የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ ከነገ ጀምሮ የዘመቻ ስራ ይከናወናል ፡፡

"በአሁኑ ወቅት አለማቀፍ ኢንቨስተሮች በብዛት ትኩረት እያደረጉ ያሉት የኮቪድ -19 ክትባት ተደራሽ በሆነባቸው አገራት ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ" ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ክትባቱ በስፋት መሰጠቱ በኢንቨስትመንት  ዘርፍ  የሚሰማሩ የውጭ ሀገራት ባለሃብቶች ቁጥር በማሳደግ የኢኮኖሚ ዘርፉን ለማጠናከር ጭምር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ጊዜ  ቢቀንስም ቫይረሱ ባህሪውን በመቀያየር እንደ አዲስ ሊያንሰራራ ስለሚችል ማህበረሰቡ ስጋቱን ከግምት በማስገባት ክትባቱን በመውሰድ እራሱን ከበሽታው ጉዳት እንዲጠብቅ ጠቁመዋል።

ካሁን ቀደም በክልሉ 72ሺ 629 ዜጎች ክትባቱን መውሰዳቸውና የነበረው ስርጭት በመቀነሱ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ክትባቱን ያልወሰዱትን ሰዎች ጨምሮ ፣አንደኛ እና  ሁለተኛ ዙር የወሰዱ  ሁሉም ክትባቱን እንዲወስዱ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የግልም ሆነ የመንግስት ሁሉም ተቋማት ሰራተኞቻቸው  ክትባቱን እንዲወስዱ በማድረግ የበኩላቸውን  ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል ፡፡

የክትባት ዘመቻው ከነገ  ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥና ህብረተሰቡ ለጤና ባለሞያዎች

  አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም