በህግ ማስከበር ዘመቻው ሰላማችን በመረጋገጡ በነጻነት መንቀሳቀስ ችለናል--የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች

148

ከሚሴ ግንቦት 30/2014 (ኢዜአ) ‘’መንግስት እየወሰደ ባለው ጠንካራ ህግ የማስከበር ዘመቻ ያለ ስጋት በሰላም ወጥተን ለመግባት ችለናል’’ ሲሉ የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ  የህግ ማስከበር ዘመቻውን የሚደግፍና አሸባሪውን ሸኔ የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አህመድ በሽር ለኢዜአ እንዳሉት፣ የሴራ ፖለቲከኞች ህዝብን በሃይማኖትና በብሔር ለመከፋፈል በሚቀሰቅሱት ሁከትና ብጥብጥ የሰላምና ጸጥታ ስጋቶች አጋጥሟቸዋል።

በየጊዜው ሲፈጸሙ የነበሩ ግድያ፣ አፈና፣ ዘረፋና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት በአካባቢያቸው ያለ ስጋት ተንቀሳቅሰው ለመስራት ተቸግረው እንደነበር ተናግረዋል።

አቶ አህመድ "በአሁኑ ወቅት በአካባቢያችን በሰፈነው ሰላም በነጻነት ወጥተን መግባት ችለናል፤ የእለት ተእለት ስራችንንም ያለ ስጋት እያከናወን ነው" ብለዋል።

ህግ የማስከበር ዘመቻው እንዲጠናከርና የአሸባሪው ሸኔ አከርካሪ እንዲሰበር ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የህግ የበላይነት ባለመከበሩ ሸኔን ጨምሮ ጉልበተኞች የህዝብንና የመንግስትን ንብረት ሲዘርፉና በዜጎች ላይ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር የገለጹት ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኢሳ ሁሴን ናቸው።

"በህገወጦች ሲፈጸም በነበረው ድርጊት ከማዘን ባለፈ በመንግስት ህግ የማስከበር አቅም ላይ ጥርጣሬ ፈጥሮብን ነበር" ያሉት አቶ ሁሴን፣ ህገወጥ እንቅስቃሴው የደህንነት ስጋት ሆኖብኝ ነበር" ብለዋል።

"የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ለመንግስት ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት የህግ ማስከበር ዘመቻው በመካሄዱ በሰፈነው ሰላም ተደስተናል" ነው ያሉት።

ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብና የህዝብ ጠላት የሆነውን ሸኔን ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

"ህግ የማስከበር ዘመቻውን ደግፈን በራሳችን ተነሳሽነት ሰላማዊ ሰልፍ የወጣነው አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን በጋራ ለማስቀጠል ነው" ሲሉም አክለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ የመንግስትን ሆደ ሰፊነት አቅም እንደሌለው የቆጠሩ አገር አፍራሾች በህዝብ ላይ የተለያየ በደል መፈጸማቸውን አስታውሰዋል።

ከህዝብ ለተነሳው ተደጋጋሚ ጥያቄ መንግስት መልስ ለመስጠትና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ህግ የማስከበር ዘመቻውን በተጠናከረ ሁኔታ እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘመቻው የሸኔ አባላትን ጨምሮ በነፍስ ግድያ፣ በስርቆት፣ በዝርፊያ፣ በህግ ወጥ የገንዘብና መሳሪያ ዝውውር፣ በሰዎች ዝውውርና ሌሎች መሰል ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ተጠርጣሪዎች ለህግ እንዲቀርቡ በማጋለጥ በኩል ድርሻው የጎላ እንደነበር ጠቁመው፣ በቀጣይም ይህ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ለልማት፣ ለአንድነትና ለሰላም ፀር የሆነውን አሸባሪውን ሸኔን ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ህዝብን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በሰልፉ ላይ የከሚሴ ነዋሪዎች፣ የሃይማት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የዞኑ አመራሮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

ህግ የማስከበር ዘመቻውን የሚደግፍና አሸባሪውን ሸኔን የሚያወግዝ ተመሳሳይ ሰልፍ በባቲ እና ሰንበቴ ከተሞችም ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም