ለ3ኛው ዙር የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ ውጤታማነት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሃላፊነት አለባቸው - ሚኒስቴሩ

123

አዳማ ግንቦት 30/2014(ኢዜአ)... ሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይሬስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ሃላፊነት በመወጣት እንዲያግዙ የጤና ሚኒስቴር ጠየቀ።

ከሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚጀመረውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በ3ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዘመቻ ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለመከተብ ታቅዷል።

በዚህም ከሀገራችን ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑ ዜጎችን ለመከተብ ግብ መቀመጡን ነው የገለጹት።

በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር ዘመቻ 24 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን መከተብ መቻሉን የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ በዚህም የበሽታውን ስርጭት መግታት መቻሉን አመልክተዋል።

የ3ኛው ዙር የክትባት ዘመቻ በዋነኛነት በግጭት ውስጥ የቆዩ የሀገራችንን አካባቢዎች መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለፁት ዶክተር መሰረት፤ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ሁሉ ክትባቱ እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።

አንድ ዙር ብቻ የተከተቡ ዜጎች የ3ኛውን ዙር ክትባት መውሰድ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

ዘመቻው የተሳካ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ዶክተር መሰረት፤ በተለይ ህብረተሰቡን በማንቃትና ስለክትባቱ ጠቃሚነት በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በዚህም የህዝብና የግል የመገናኛ ብዙሃን አካላት ሙያዊ ዕገዛና ድጋፍ በማድረግ ረገድ ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የተቀናጀና ዘርፈ ብዙ ምላሽ በማድረግ፣ የኮቪድ መከላከያ ፕሮቶኮልና መመሪያዎቹን በሁሉም ደረጃ ተፈፃሚ በማድረግ ሊደርስ የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መቋቋም መቻሉን አስታውሰዋል።

አሁንም ሀገራችንን ከበሽታው ስጋት ነፃ ለማድረግ ማህበረሰቡ እንዳይዘናጋ በማንቃትና ክትባት እንዲወስድ በማድረግ ሁላችንም ሀገራዊ ሃላፊነት መወጣት አለብን ብለዋል።

የሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የክትባት ቡድን አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው ናቸው።

"በጤና ተቋማት ብቻ የሚሰጠው ክትባት የተፈለገውን ያህል ሊያስኬድ አልቻለም" ያሉት አስተባባሪው ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ የሚካሄደው 3ኛው ዙር ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሙሉ አቅማቸው ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የ3ኛውን ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻን ለማሳካት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከህዝብና ከግል የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም