የፀረ-ወባ መድሃኒት እና የአጎበር ስርጭት በማካሄድ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው-የጤና ሚኒስቴር

252

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ የፀረ-ወባ መድሃኒት እና የአጎበር ስርጭት በማካሄድ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡


ሚኒስቴሩ ከኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በወባ ስርጭት፣በኮሮና ቫይረስና በዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት፣ በደቡብ፣ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የወባ ወረርሽኝ መጨመሩን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።  

ባለፉት አስር ወራት የወባ ምርመራ ከተደረገላቸው ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ውስጥ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑት ላይ በሽታው መገኘቱን ገልጸዋል።  

ይህም ከ2013 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

ሚኒስትር ደኤታው እንዳሉት፤ ለወረርሽኙ መስፋፋት ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩ፣ድርቅ ተከስቶባቸው የነበሩ አከባቢዎች ላይ ዝናብ መጣሉ፣ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ለወረርሽኙ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

በተጨማሪ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀምና የጸጥታ ችግር በጋጠመባቸው ቦታዎች ላይ የመከላከል ስራው መቀዛቀዙ ለወረርሽኙ መስፋፋት አዎንታዊ ሚና መጫዎቱን ገልጸዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህሙማንን ማከም የሚያስችል የጸረ ወባ መድሃኒት ተሰራጭቷል ብለዋል።

በተጨማሪ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን አጎበር ተገዝቶ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፈጣን የወባ ምርመራ  ማድረግ የሚያስችሉ ቁሳቁሶች መሰራጨታቸውንም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ላይ መዘናጋቶች እያታዩ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤  ይህም በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን አብራርተዋል።

ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ጋር በተያያዘም በሽታው በ30 አገራት ላይ መከሰቱን ጠቁመው፤ በሽታው በኢትዮጵያ መከሰቱን የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም ነው ያሉት፡፡

በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ቅድመ ጥንቃቄዎች እየተደረጉ መሆኑንም አክለዋል።

ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ከወዲሁ ማድረግ እንዳለበትም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም