በከተማዋ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

117

ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ተግባራትን ለመከላከል የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ለኢዜአ እንደገለጹት በመዲናዋ ከመሠረታዊው የኑሮ ውድነት ምክንያቶች ጎን ለጎን ችግሩን የሚያባብሱ በርካታ መንስኤዎችን አሉ።  

ከእነዚህም መካከል በፍጆታ እቃዎች ላይ የሚስተዋለው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና ሕገ-ወጥ የንግድ ሥርዓት መንሰራፋት ትልቁን ሥፍራ እንደሚይዙ ገልጸዋል።  

ያልተገባ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር እንዲሁም በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ አለመሆንና ሌሎች ተያያዥ አባባሽ ጉዳዮች መኖራቸውን ነው ያብራሩት።

ይህንንም ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ የፍጆታ እቃዎችን በስፋትና የተሻለ የዋጋ ተመን በማቅረብ ችግሩን ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፍጆታ እቃዎችን በሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በማቅረብና የእሁድ ገበያዎችን በማስፋት ገበያውን  የማረጋጋት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ጠቁመዋል።

የቤት ኪራይ ዋጋን ለማረጋጋት የዋጋ ጭማሪ ላይ ገደብ መጣሉን አስታውሰው የትራንስፖርት ችግሩን ለማቃለልም የትራንስፖርት አማራጮችን የማቅረብ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የኑሮ ውድነቱ ባለበት እንዲቆምና እንዲረጋጋ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።  

ጎን ለጎንም የከተማ ግብርናን ባህልና ልምድ ለማድረግ እየተሰሩ ባሉ ጅምር ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በከተማ ግብርና የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት ተሞክሮን በመተግበር በተከናወኑ ሥራዎች በቀላሉ የማምረት እድል መኖሩን መገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም ጊዜና ቦታን የማይፈጁ በቀላሉ መመረት የሚችሉ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት የቤት ውስጥ ፍጆታን መሸፈን እንደሚቻል ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

በዘርፉ የተገኙ መልካም ውጤቶችን በማስቀጠል ዘርፉን ለማሳደግ ከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያጠናክርም ገልጸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማ ግብርና በማጠናከር በዘርፉ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚሰራም ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አረጋግጠዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም