የልማት ድርጅቱ በዋግ ኽምራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገ

85

ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አስተዳደር በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሃት ለተፈናቀሉ ወገኖች 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገ፡፡

የልማት ድርጅቱ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው ጌቴ እንዳሉት የልማት ድርጅቱ በክልሉ ከሚሰራው የልማት ስራዎች ጎን ለጎን የማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

በዚህም በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በዋግ ኽምራና ሰሜን ወሎ ዞኖች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ድጋፍን አቅርቧል።

በዛሬው እለትም በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 500 ኩንታል የአልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ተመሳሳይ መጠን ያለው ድጋፍም በሰሜን ወሎ ዞኖች ለሚገኙ ተፈናቃዮች መላኩን አመልክተዋል።

ከድጋፉ ውስጥም 100 ኩንታል ፋፋ፣150 ኩንታል ማካሮኒ፣ 200 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት እና 5 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ይገኝበታል።

አስተዳደሩም ከልማት ስራዎች ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ ስቡህ ገበያው በበኩላቸው የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ያደረጉት ድጋፍ የወገንተኝነት ማሳያ ነው።

ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረጉ ድጋፍ በተቀዛቀዘበት ወቅት የተደረገ ድጋፍ የተፈናቃይ ወገኖችን ወቅታዊ የምግብ አቅርቦት ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይም ሌሎች የልማት ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኞች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ88 ሺህ በላይ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ፣ወለህና ፅፅቃ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም