የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል--ጤና ሚኒስቴር

106

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ  ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን በወባ ወረርሽኝ ፡በኮሮና ቫይረስና የዝንጀሮ  ፈንጣጣ ዙሪያ መግለጫ  ሰጥተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ደኤታ  ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የወባ ወረርሽኝን በመከላከል  ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እየተስተዋለ ነው፡፡

ባላፉት አራት  ወራት በተለይ  በደቡብ ክልል፡በአማራ፡ኦሮሚያ፡ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጰያ ክልሎች ወረርሽኙ መጨመሩን  ተናግረዋል፡፡

አጎበር  በአግባቡ  አለመጠቀም፣ የአመራሩና ህብረተሰቡ መዘናጋት፣ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የነበረው የጸጥታ  ችግር ለወረርሽኙ መስፋፋት በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪ ድርቁን ተከትሎ የተከሰተው ከባድ ዝናብ ለወባ ወረርሽኝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ወርሽኙን ለመግታት  ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት  እየተሰራ መሆኑን  ገልጸው፤ ኀብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ  በኩል  የዝንጀሮ  ፈንጣጣ  በኢትዮጵያ  መከሰቱን  የሚያሳይ  መረጃ እንዳልተገኘ ጠቁመው፤ ነገር ግን ከወዲሁ ቅድመ  ጥንቃቄዎች እየተደረጉ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም