የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ዝናብ አጠርና ቆላማ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃን ለማልማት የሚያስችል የ210 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ

99

ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ በብዛት በሚገኝባቸው ዝናብ አጠርና ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃን ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የ210 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ገንዘቡ በኢትዮጵያ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃን በማልማት ለመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም ለመስኖ ልማት ለማዋል ለተቀረጹ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ነው፡፡

ፕሮጀክቶቹ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር በ5 ዓመታት ውስጥ የሚተገበሩ ሲሆን ዝናብ አጠርና ቆላማ አካባቢ የሚኖሩ የሀገሪቱን ዜጎች ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ ዛሬ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ከዓለም ባንክ ልዑክ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን የድጋፍ ስምምነቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ከተፈረመና በሀገሪቱ ፓርላማ ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ ድጋፉ ዝናብ አጠር በሆኑና በድርቅ በሚጠቁ አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖች የሚጠቅም ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር ፕሮጀክቶቹን እንደሚመሯቸው ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶቹ በምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃ በብዛት በሚገኝባቸው፣ዝናብ አጠርና ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አካል መሆናቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም