በጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ ድጋፍ እየተደረገ ነው

1

አምቦ ፤ ግንቦት 29/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች መቋቋሚያ የምግብ እህልና የቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የመጠባበቂያ ፈንድ አሰባሰብና አስተዳደር የአደጋ ምላሽና መልሶ ማቋቋም የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሸለመ ፌዬራ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉ የተገኘው በአከባቢው ካሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ፣ ከቀይ መስቀል፣ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከነዋሪዎችና ባለሃብቶች መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከድጋፉ መካከል ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የምግብ እህል፣ የጊዜያዊ መጠለያ ሸራዎች ፣ አልባሳት የንጽህና መጠበቂያና የተለያዩ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ የተደረገው በጸጥታ መደፍረስ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ  በባኮ ትቤ ፣ ጅባት ፣ ኖኖ፣  ዳኖ፣  እና ሜታ ወልቂጤ ወረዳዎች ነዋሪ ለሆኑ ከአምስት መቶ በላይ አባወራዎች ነው፡፡

የተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን የምግብና አልባሳት ችግር የሚያቃልል መሆኑን ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ ቀጣይነት እንዳለው ገልፀው፣ ድጋፉ የተገኘው ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ ከወረዳዎች፣ ከፌዴራል መንግስትና ከኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር የአምቦ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ መኮንን ባለፉት ሁለት ወራት ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶችን  በኖኖ እና ጅባት ወረዳዎች ለችግር ለተጋለጡ 200 አባወራዎች መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ልገሳው ለችግር የተጋለጡ ወገኖች እስከሚቋቋሙ ድረስ ቀጣይነት እንዳለውም አመልክተዋል፡፡  

በኖኖ ወረዳ የቢሎ አቦ ቀበሌ ነዋሪ ምናሴ በፍቃዱ በጸረ ሰላም ሃይሎች ቤት ንብረታቸው ወድሞባቸው ለችግር መጋለጣቸውንና የብርድ ልብስ፣ የመጠለያ ሸራ እና የንጽህና መጠበቂዎችን ድጋፍ ከቀይ መስቀል ማህበር  ማግኘታቸውነ ተናግረዋል።

የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ለቤት መስሪያ የሚሆኑ ቆርቆሮዎችና ሌሎች ድጋፍ እንዳደረጉላቸውም ጠቅሰዋል፡፡