ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ ፍሬአማ እንዲሆን ሁሉም ሊዘጋጅ ይገባል — የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

2

ግንቦት 29/2014 (ኢዜአ) ሁሉም ነገር በጉልበት እንደማይፈታ ከታሪካችን በመማር ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ፍሬአማ ለማድረግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊዘጋጅ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ከአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በኮሚሽኑ ሃላፊነትና ተግበራት ላይ ዛሬ በባህዳር ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንዳሉት የሀገርና የህዝብ አንድነትን ማጽናት የሚቻለው  የችግሮች መፍቻ አሰራርን በዘላቂነት መዘርጋትና መተግበር ሲቻል ነው።

አሰራሩ በየጊዜው ጽንፈኛ አካላት በሚፈጥሩት ግጭት የሚደርሰውን የሰው ህይወት መጥፋት፣ የሃብትና ንብረት መውደምና ሌሎች ችግሮች በዘላቂነት ለማስቆም ዋና መፍትሄ መሆኑ አለበት ነው ያሉት።

“በአገራችን ባለፉት ዓመታት ከተፈጠሩ ችግሮች በመማር ሌላችግር እንዳይፈጠር መስራት አለብን” ያሉት ዶክተር ይልቃል ለዚህም የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማውና ግቡ እንዲሳካ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ድርጅቶች፣ ህብረተሰቡ፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

ኮሚሽኑ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ሁሉ የክልሉ መንግስትና በስሩ የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶክተር ይልቃል አረጋግጠዋል።

“በኢትዮጵያ ውይይት፣ ሽምግልናና እርቅ ከጥንት ጀምሮ የመጡ የታሪክ እሴቶች ናቸው” ያሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሰብሰቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ  አንዳንድ ጊዜ ሀገራዊ እሴችን ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር የመደባለቅ ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉ ነው የጠቀሱት።

የኮሚሽኑ ዋና ዓላማም በሀገርቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ተቃርኖዎችን በማጥበብ አንድነትን ለማጽናት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ተሳታፊዎችን መለየት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማካተት፣ አደረጃጀትና አሰራርን በመዘርጋት ለምክክሩ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን በመሰብሰብ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

የውይይቱን ጽንሰ ሃሳብ እስከታች ድረስ በማስረጽ ከድርድር፣ ከሽምግልና፣ ከማስታረቅ ጋር ያለውን ልዩነት በማስገንዘብ በአዋጅ የተሰጡትን ተግባራት ለማሳከት በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያስገነዘቡት።

ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር የተካሄደው ውይይት ስጋቶችን በማንጸባረቅና መደረግ ያለባቸውን ጉዳዮች በማመላከት ለምክክሩ ስኬት አስፈላጊው ግብዓት የተገኘበት መሆኑንም ፕሮፌሰር መስፍን አብራርተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ አይናአለም ንጉሴ በበኩላቸው የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ መሆን ለመጪው ትውልድ ጭምር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ውይይቱ ሀገርና ህዝብ ያለችግር እንዲቀጥሉና በኢኮኖሚ የጠነከረ ፣በማህበራዊ መስተጋብሩ የሰለጠነ  አገር የመገንባት ሂደትን ለማፋጠን የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ሁሉም የክልል ቢሮ ሃላፊዎች፣ የወጣት፣ የሃይማኖት አባት፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ተመልክቷል።