በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

153

ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ገለጸ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አገራዊ ፋይዳ ያለው ዘላቂ ተግባር አድርጎ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ።ለዚህ ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ አስፈላጊ በመሆኑ አገራዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምጣኔ ሃብታዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ያሉ ጉድለቶችን በመሙላት ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም አገልግሎቱ ከዘመቻ ባለፈ ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት ተቋማዊ በሆነ መልኩ በዘላቂነት እንዲቀጥል ለማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

የፖሊሲ ማዕቀፉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰሩ የመንግሥት ተቋማት፣የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚመሩበት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ለምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ እድገት ፤ለሰላም ግንባታ እንዲሁም ለአገር ጠቀሜታ ያለውን ጉልህ ሚና በሚገባ እንዲወጣ ለማድረግ በፖሊሲ መመራቱ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሲቪል ድርጅቶችን የሚገድቡ ሕግጋት መሻሻላቸውን ተከትሎም በርካታ ሀገር በቀልና የውጭ ሲቪል ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት 2 ሺህ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት 1 ሺህ 800 ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪል ድርጅቶች እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ላይ በድምሩ 3 ሺህ 800 ድርጅቶች በፌደራል ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቷቸው በሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ በአገራዊ ምርጫ ሂደት፣በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል፣ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና በሌሎችም አገልግሎቶች ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም