የግብርና ምርታማነትን የሚጨምሩ አስር መርሃ-ግብሮች እየተተገበሩ ነው–የግብርና ሚኒስቴር

4

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2014 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ የግብርና ምርታማነትን የሚጨምሩ አስር መርሃ -ግብሮች እየተገበሩ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

መርሃ -ግብሮቹ በስንዴ ልማት የተጀመረውን ስራ ወደ ሌሎች ዘጠኝ ምርቶች የሚያሳድጉ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ 

ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን የ2014 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

በዚህም የአስር አመቱን የልማት እቅድ እና የተሻሻለውን ፖሊሲ በትኩረት ለመተግበር የሚያስችሉ 10 አገራዊ መርሃ-ግብሮች ተቀርጸው በትግበራ ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል።

መርሃ ግብሮቹም በአገር ውስጥ ገበያ ያለውን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም በማጥበብ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር እና በምግብ ንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦች አቅርቦትን ማሳደግ ዓላማ ያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪ የምግብና ስርአተ ምግብ ዋስትና የማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካትና አገራዊ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ከመርሃ-ግብሩ ዓላማዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

መርሃ -ግብሮቹ በስንዴ ልማት የተጀመረውን ስራ ጨምሮ የሩዝ፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡናን ያካተቱ እንደሆኑም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን በላይ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ 8 ነጥብ 21 ሚሊዮን መላኩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ 2 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል።

በግብርና ወጪ ምርቶች ከተገኘው ገቢ ቡና 45 በመቶ እንዲሁም አበባ 19 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፤ ቀሪውን ደግሞ ሌሎች የግብርና ምርቶች እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በ2014 በጀት ዓመት የበልግ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ለማዘጋጀት ታቅዶ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን መታረሱን አብራርተዋል።

ከታረሰው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ወይም የእቅዱን 82 በመቶ የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።

የበልግ አምራች በሆኑ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያጋጠመው ድርቅ በበልግ ልማት ላይ ተጽእኖ በማድረጉ ከተዘጋጀው መሬት ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በዘር ሳይሸፈን መቅረቱን ጠቁመዋል።

ግብርና ሚኒስቴር በጦርነትና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የገንዘብና የአይነት ድጋፎችን ማድረጉንም ሚኒስቴሩ ገልጸዋል።