ክልሉን በብዝሃ ከተሞች ለማደራጀት እየተሰራ ነው -- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተዳድር

82

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 29/2014 (ኢዜአ) የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ክልሉን ብዝሃ ከተሞች የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተዳድር አስታወቀ ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ህዝቡ በራስ ፍላጎትና ወንድማማችነት የጋራ ክልል ለመመስረት ሲወስን ሰፊ የልማት ጥያቄዎችን በመያዝ ነው።

በጋራ የመልማት ጥያቄን በቅርበት መፍታት እንዲቻል ክልሉ አራት ማዕከላት እንዲኖሩት በተወሰነው መሠረት ለማደራጀት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

"በክልሉ ህገመንግስት የጸደቀውን ባለብዝሃ ማዕከልነት ተግባራዊ ለማድረግ ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ አካላትን የያዘ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደስራ ተገብቷል" ነው ያሉት።

"ህብረተሰቡ የብዝሃ ማዕከላትን በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ የህዝብ ሃላፊነት ከተሰጠው መንግስት ውጭ በማኅበራዊ ድረገጾች ለሚነዙ አሉባልታዎች መቀበል የለበትም" ብለዋል።

የክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ተዘራ ወልደማሪያም የክልሉ መንግስት የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ከተሞች የሚደራጁ ተቋማትን ክላስተር የማድረጉ ስራ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን  በመውሰድና በጥናት ላይ የተመሰረተ ልየታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

"አደራጅ ኮሚቴው እያካሄደ ያለውን ጥናት ሲጠናቀቅ ለውይይት እንደሚቀርብና ለግብአት የሚሆኑ ሃሳቦችን ካሉ  በማካተት አሳታፊነቱን የሚያረጋግጥ ነው" መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማደራጀቱ ስራ የህዝቦችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ህዝቡ ለአላስፈላጊ አጀንዳዎች ጆሮ መስጠት እንደሌለበትም ጠቁመዋል።

ክልሉ ተግባሩን ከመደበኛ የልማትና የአስተዳደር ስራዎች ጎን ለጎን እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

መጪው የክረምት ወቅት ሰፊ የግብርና ልማት ስራዎች የሚከናወኑበት በመሆኑ የክልሉ ህዝብ የአካባቢውን ሰላም እየጠበቀ የልማት ስራዎችን ላይ እንዲረባረብ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም