"ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን አንገብጋቢ ችግሮች በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እየሰራን ነው"--ከንቲባ አዳነች አቤቤ

106

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2014(ኢዜአ)"ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን አንገብጋቢ ችግሮች በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እየሰራን ነው" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባዋ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ በ54 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ለሚገነባው የጃራ አባገዳ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት የገዥው ፓርቲ ብልጽግና አንደኛ ጉባኤ መጠናቀቅን ተከትሎ ከመዲናዋ ነዋሪዎች በተደረገው ውይይት ሕብረተሰቡ ቢፈቱ ያላቸውን ጥያቄዎች ማንሳቱን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የትምህርት ዘርፉን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር አስታውሰው፤ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት መሰረተ-ልማት እንዲስፋፋ መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከኅብረተሰቡ የተነሱ ችግሮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በዛሬው እለት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የጃራ አባገዳ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ የዚሁ ሥራ አካል መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በህገ-መንግስቱ  ተቀባይነት ያገኘ መብት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ከዚህ አኳያ ትምህርት ቤቱ የአካባቢው ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ፤ የማስፋፊያ ግንባታው ትምህርት ቤቱ መማር ማስተማሩን በሚፈለገው ደረጃ እንዲሰጥ እንደሚያግዘው ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ የአካባቢው ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩና ባህላቸውን እንዲያውቁ የሚያስችል አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የቦሌ ክፍለ ከተማ  ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለምፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው፤ የጃራ አባገዳ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የአስተዳደር ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማስፋፊያ ግንባታው በ54 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፤ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ  ከሦስት ዓመት በፊት የተመሰረተ ሲሆን፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ 405 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ሲኖረው የማስፋፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ ይህንን ቁጥር ወደ 1 ሺህ 500  ከፍ ማድረግ ያስችላል ነው የተባለው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም