ሀገር በቀል የሰላም እሴቶች አንድነትን ለማጠናከር - ምሁራን

350

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 29/2014 (ኢዜአ) ሀገር በቀል የሰላም እሴቶችን በማጎልበት አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው ዘርፎች የራሷ ሀገር በቀል እውቀት እንዳሏት ምሁራኑ ጠቅሰዋል።

አገር በቀል እውቀቶቹን  የየአካባቢው ማህበረሰብ በጠባቡ ሲጠቀምባቸው ቢቆይም በጥናት ወጥተው ለሰፊው ህዝብ ግልጋሎት ያልዋሉና በሳይንሱ ቢደገፉ ደግሞ አንዳንዶቹ ለዓለም እሴት እስከመሆን ደረጃ የሚደርሱ መሆኑም ተመላክተዋል።

ማኅበረሰቡ ሰላምን አስጠብቆ አብሮነቱን ለማጎልበት የሚያስችሉ ጠንካራ ባህላዊ የሰላም እሴቶች እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ሳይንስ መምህርና የሀገር በቀል እውቀት ልማትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ መምህር አብለል ተከስተ ተናግረዋል።

በየአካባቢው የሚገኙ የማኅበረሰቡ ነባር የአኗኗር ዘይቤዎችን በማልማት መጠቀም ከተቻለም ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለው የሰላም እጦት ተፈቶ አንድነቷ እንደሚፀና ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ በቋንቋ ብዝሃነት ውስጥ የሚያግባቡና አንድ የሚያደርጉ እንደ እርቀ ሰላም ያሉትን ጨምሮ አብሮ መብላትና መጠጣት፣ እንግዳ መቀበልና የመቻቻል መልካም እሴቶች ያሏት ሀገር ነች" ሲሉም አክለዋል።

"ያሉንን መልካም እሴቶች በዜሮ አባዝቶ የእኛ ያልሆነውን ልማድ መገለጫ አድርጎ መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እየተመለከትን" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም አባቶች የሚሉትን የሚሰማ፣ ሰው አክባሪና ግብረ ገብ ያለው ትውልድ ለማፍራት የሚያስችሉ ኢትዮጵያዊ ሥርዓትን ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማየት ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመከባበር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ሀገር በቀል እውቀቶቹ ለአንድነትና ሰላማችን ያላቸው ፋይዳ ትልቅ ቢሆንም በአግባቡ ባለመያዛቸው ሊያመልጡ እንደሚችሉም ብለዋል።

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ የተሰጠው ሀገራዊ ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በህብረተሰቡ ወስጥ ይበልጥ እንዲሰርጽና ለግልጋሎት እንዲውል ግን ተከታታይነት ያለውን ግንዛቤ መፍጠርና መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርስቲው የታሪክ መምህር አለማየሁ አብርሃም በበኩላቸው "ኢትዮጵያ የሚያለያዩ ሳይሆን አንድ የሚያደርጉ በርካታ ታሪኮችና እሴቶች አሏት" ብለዋል።

ያልነበሩትን የልዩነት ትርክቶች በመንዛት አንድነቷን ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸው፤ እየተፈጠሩ ያሉ ያለመደማመጥ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የጋራ ባህላዊ እሴቶቻችን መዳበር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚነዛው ሐሰተኛ መረጃ በአገሪቱ ተገቢ ያልሆነ ገጽታ ለመፍጠር ቢሞክርም  ማኀሰበረሰቡ ግን እንደ ትናንቱ የአብሮነት ባህሉን ጠብቆ እየኖረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ባሉበት አካባቢ በማኅበራዊ ጉዳዮች ልዩነትን ሳይፈጥሩ በሀዘንና ደስታ ተጠያይቀው፣ ችግሮቻቸውን በመነጋገርና በባህላዊ ዳኝነት እየፈቱ የኖሩና ወደፊት መቀጠል የሚችሉ ህዝቦች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ጠቃሚ ያልሆኑ እንግዳ ድርጊቶችን "ነውር ነው" በማለት እየተቃወሙ አንድ የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊ ወግና ሥርዓቶችን ማጎልበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ምሁራኑ "የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን የመፍትሄ ሀሳብ መፍታት እንችላለን" በማለት የራስን በማጠናከሩ ላይ ይበርታ በማለትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም