ከፍተኛ የክረምት ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ከወዲሁ በማዘጋጀት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል

110

ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመጪው ክረምት ወቅት ከፍተኛ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ከወዲሁ በማዘጋጀት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚወጡ ትንበያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ላይ  መሆኑንም አስታውቋል።

ትንበያዎች እንደሚያመለክቱት በክረምቱ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይጠበቃል።

የኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና  የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያ ታምሩ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ላሊና ባስከተለው የአየር ጠባይ ለውጥ በበልግና መኸር ወቅቶች ደረቃማ ወራት በዝተው እንዲስተዋሉ አድርጓል።

በመሆኑም በክረምት ወቅት በተለይ በሐምሌና ነሐሴ ወር ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች መጠቆማቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ  የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ከወዲሁ በማዘጋጀት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎችም ኢንስቲትዩቱ  በሚያወጣው መረጃ ላይ የተመሰረቱ ምክረ-ሃሳቦችን አስቀድመው ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው፤ በመጪው ክረምት በሚኖረው ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ይኸው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በሰብል ላይም ጉዳት ከማድረሱ በፊት አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል ትንበያዎችን በወቅቱ  ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚሁ ወቅት የተሻለ የሰብል እድገት የሚጠበቅ በመሆኑም አርሶ አደሩ የአረም ቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለይ ከማሳ ውጭ የሚሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የውሃ መቀነሻና የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀት ጨምሮ ተመሳሳይ የመከላከያ ዘዴዎችን መተግበር እንደሚገባም ነው ያነሱት።

"አርሶአደሩ በበልግ የመጨረሻው ወቅት የሚኖረውን ዝናብ ለክረምት ማሳ ዝግጅት መጠቀም አለበት" ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ የዘር ወቅት በመሆኑም ማሳን በዘር ለመሸፈን ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅበትም መክረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም