የምክክር ኮሚሽኑን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሀገር አንድነትን ማስቀጠል ይገባል

4

ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን መቋቋም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዋና ዋና ሃገራዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሀገር እና ህዝብ አንድነትን ለማስቀጠል በጋራ መስራት እንደሚገባ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስገነዘቡ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ከአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር የትውውቅ መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂደዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም መልካም አጋጣሚ ነው።

የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም የሚስተዋሉ ዋና ዋና ሀገራዊ የችግሮችን በውይይት በመፍታት የሀገርና ህዝብ አንድነትን ለማስቀጠል ሁሉም ህብረተሰብ ትብብር ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ፣ ስልጣኔና ባህል ያላት ታላቅ ሀገር ናት” ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ለዘመናት ተፈቃቅሮና ተከባብሮ የኖረውን ህዝብ እርስ በእርስ በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ ቡድኖች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ኮሚሽኑ በክልሉ ለሚያካሂዳቸው የምክክር መድረኮች አስፈላጊው ትብብር ይደረጋል ብለዋል።