በዞኑ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

94

ደብረ ማርቆስ ግንቦት 28/2014(ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ገልጿል።

የመምሪያው ሃላፊ ወይዘሮ ሙሉነሽ ውበቴ  ለኢዜአ  እንደተናገሩት  የዞኑን  ኢንቨስትመንት በማጠናከር 185 የሚሆኑ ማህበራትና ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክታቸውን ቀርጸው አስገብተዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ5 ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 94 ፕሮጀክቶች ፈቃድ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹን ወደ ስራ ለማስገባትም ከ35 ሄክታር በላይ መሬት ማስረከብ መቻሉን ጠቁመው፤ ከእነዚህ 23ቱ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት በመሸጋገር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ፈቃድ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶችም ግንባታቸውን ሙሉ በሙሉ አጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ   ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ተመላክቷል።
አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ግብርናና ሌሎች የስራ መስኮች ደግሞ ኢንቨስተሮቹ የተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መሆናቸውን ወይዘሮ ሙሉነሽ አብራርተዋል።
በደብረ ኤሊያስ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ባለሃብት አቶ ትዕዛዙ ዳምጠው እንዳሉት  ከ25 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ የዱቄትና የእንስስት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባተ ፈቃድ ወስደው ቦታ ተረክበዋል።

በአሁኑ ወቅትም የፋብሪካውን ግንባታ በማጠናቀቅ ማሽን ለመትከል በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ወደ ማምረት እንደሚሸጋገሩ ተናግረዋል።
ፋብሪካው ወደ ማምረት ሲሸጋገርም ከ30 በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች በቋሚና በጊዜያዊነት የስራ እድል እንደሚፈጥሩም አስረድተዋል።
የባሶ ሊበን ወረዳ የኮርክ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዓለሚቱ ዳረንጎት በበኩላቸው ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ በእንጨትና ብረታ ብረት ዘርፍ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት ወደ ስራ የገቡት ከ360 በላይ ፕሮጀክቶች ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚ እና በጊዚያዊነት  የስራ እድል የተፈጠረ መሆኑን ከዞኑ የተገኘው መሆኑ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም