የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው

130

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ በሁለተኛ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣዩ ዓመት በሌሎች አዳዲስ የትምህርት መስኮች ማስተማር ለመጀመር ተዘጋጅቷል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከአገሪቷ ከሁሉም አካባቢዎች የፖሊስ አባላትንና መኮንኖችን በመቀበል በተለያዩ የትምህርት መስኮች አስተምሮ በማስመረቅ ዘመናትን የተሻገረ ስራ በመስራት ይታወቃል።

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ በሁለተኛ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ተሾመ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማስፈን ከአገራት አቻ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የተለያዩ ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።   

ከስምምነቶቹ አንዱ አገራቱ ያላቸውን የፖሊስ ኃይል በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ማዘመን አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ የሚያስተምረውም በዚሁ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።        

በመሆኑም በሚቀጥለው ዓመት የጎረቤት አገር ጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ በሰላምና ደህንነት የትምህርት መስክ በሁለተኛ ድግሪ ለማስተማር ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከሶማሌ ላንድ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሩዋንዳ የፖሊስ አባላትን ተቀብሎ ማስተማሩን ጠቁመው፤ ይህም በቀጣናው ያለውን የፖሊስ ኃይል ለማጠናከር ፋይዳው ከፍተኛ  መሆኑን ነው የተናገሩት።    

የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከገጽ-ለገጽ ትምህርት በተጓዳኝ በኦንላይን ተደራሽ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ መምህራን ጅቡቲ ሄደው ማስተማር የሚችሉበት አሰራር እንደሚዘረጋም ጠቅሰዋል።   

በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አዳዲስ መርሃ-ግብሮችን እንደሚከፍትም አስታውቀዋል።    

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በክሪሚኖሎጂና ክሪምናል ጀስቲስ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ በፖሊስ አመራር በሁለተኛ ዲግሪ የፖሊስ አባላትን እያሰለጠነ መሆኑን አስረድተዋል።

እነዚህን መርሃ-ግብሮች ወደ ሰባት ከፍ ለማድረግ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥርዓተ-ትምህርት ተዘጋጅቶ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት መጽደቁን ገልጸዋል።  

ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የሕክምና ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ቅድመ-ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ የፋርማሲና የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚጀምርም አክለዋል።   

በወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪ ሰልጣኞችን ለመቀበል ሰንዳፋ በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ኢንስቲትዩት እየተገነባ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የአመራር ኢንስቲትዩት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ረዳት ኮሚሽነሩ፤ እነዚህና መሰል ግንባታዎች የዩኒቨርሲቲውን የቅበላ አቅም የሚያሳድጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በስምንት የትምህርት አይነቶች 1 ሺህ 700 ሰልጣኞችን እያስተማረ ይገኛል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የቅበላ አቅሙን 3 ሺህ ለማድረስ ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑ ታውቋል።    

ከተመሠረተ 75 ዓመት የሞላው ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከኮሌጅነት ወደ ዩኒቨርሲቲ ካደገ አንድ ዓመት ሆኖታል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም