ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገጠር ግብርና ከ806 ሺ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል

103

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2014(ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገጠር ግብርና ከ806 ሺህ በላይ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሑሴን የሚኒስቴሩን ያለፉት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸውም በኢትዮጵያ የስንዴ መስኖ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተካሄደ ከሚገኘው ስራ ጎን ለጎን በሩዝ፣ በቅባት እህሎች፣ በአትክልት፣ በፍራፍሬ፣ በቡና በዶሮ፣ በወተት እና በስጋ ልማት ዘርፍ- ብዙ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በዘርፉ የተዘጋጁ እቅዶችን ከክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመገምገም ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል።

ሂደቱም በጥብቅ ክትትልና ዲስፕሊን እንዲመራ በማድረግ ወጪ ቆጣቢ ሆኖ እንዲካሄድ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የግብርና ምርታማነትን የሚጨምሩ ከ2 ሺህ በላይ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ 85 የሚሆኑት ላይ ሙከራ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ለግብርና ምርታማነት የሚውሉ 99 የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማላመድ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ከእነዚህ ውስጥ 12 የሚሆኑትን ለብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

የህብረት ስራ ማህበራትን የብድር ተጠቃሚ በማድረግ ረገድም አበረታች ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ከ8 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን የግብርና ኤክስቴንሽን ተጠቃሚ ማድረግ  ተችሏል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገጠር ግብርና ዘርፍ ከ806 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውን የከተማ ግብርና ልማት በማስፋፋትም ከተሞች የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት መገኛ ሆነው እንዲያገለግሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከተማ ግብርና ምርታማነትን በውጤታማነት ለመምራትም የቴክኖሎጂ አማራጮች ከማልሚያ ቦታዎች ጋር የተገናዘቡ እንዲሆኑ ስታንዳርድ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም